ቀጥታ፡

ህጎች፣ አሰራሮችና የልማት እቅዶች አካል ጉዳተኞችን በአግባቡ ተደራሽ ያደረጉ መሆናቸውን መከታተል ይገባል - በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ

አዳማ (ኢዜአ) ታህሳስ 16 /2015 ህጎች፣ አሰራሮችና የልማት እቅዶች አካል ጉዳተኞችን በአግባቡ ያካተቱና ተደራሽ ያደረጉ መሆናቸውን መከታተል እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ ገለፀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ አመራሮችና አባላትን ጨምሮ የተለያዩ የምክ ቤቱ  ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች የተሳተፉበት የአካል ጉዳተኞች ህጎች፣ አሰራሮችና የልማት እቅዶች ተፈፃሚነትና ተደራሽነት ላይ ያተኮረ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በምክር ቤቱ የተመራጭ ሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ ወይዘሮ ኪሚያ ጁንዲ በህብረተሰቡ ውስጥ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ያለውን የተሳሳተ አተያይና አስተሳሰብ ለመቅረፍ መስራት አለብን ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች የመሳተፍ እድሉን ካገኙና ተደራሽ ማድረግ ከተቻለ በብቃት የመስራት አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል።

ስለ አካል ጉዳተኞች ህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ ዝንባሌ በሚፈለገው መልኩ ያለመቀረፉ አካል ጉዳተኞችን በሚገባው ልክ ተደራሽ ማድረግ እንዳላስቻለ ገልጸው፤ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የሚወጡ ህጎችና የአሰራር ማእቀፎች፣ የእያንዳንዱ የስራ አስፈፃሚ ተቋም እቅዶች የአካል ጉዳተኞችን አካታችነት በአግባቡ የያዘ መሆኑንና በአተገባር ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመከታተልና ቁጥጥር በማድረግ የሚስተዋሉ ችግሮችን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በህጎች ተፈፃሚነት ላይ ያሉ ውስንነቶች፣ የመሰረተ ልማት ስራዎች አካል ጉዳተኞችን ያካተቱና በተገቢውን መንገድ ተደራሽ ያለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህ አመች ህጎችና መልካም ጅምር ስራዎች ቢኖሩም የአፈፃፀም ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።

የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ጀምሮ ህጎች፣ አሰራሮችና የልማት እቅዶች አካል ጉዳተኞችን በተገቢው መንገድ ያካተቱና ተደራሽ ያደረጉ ስለመሆናቸው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በመንገድ፣ በትምህርት፣ በጤናና በገበያ መሰረተ ልማት ተደራሽነት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም አሁንም በቂ ባለመሆናቸው ትኩረት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችና ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ስሞን በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞችን በማህበራዊና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ ከጥገኝነትና ተመጽዋችነት ማላቀቅ ይገባል ብለዋል።

ይሄን ለማድረግ አካታች ህጎች፣ አሰራሮችና የፖሊስ ማእቀፎች ሊኖሩ እንደሚገባ በመጠቆም።

በዚህም የአካል ጉዳተኞች የፖሊስ፣ የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች አካታችነትና ተደራሽነት በማረጋገጥ ረገድ  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ያላቸው ሚና የማይተካ ነው።

በሀገሪቷ ከስራ ስምሪት፣ ከህንፃ ዲዛይን፣ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተደራሽነ፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት አንፃር  ብዙ ህጎችና ግንዛቤዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም