ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ ረገድ ኀብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ ይገባል

ታህሳስ 16/2015 (ኢዜአ ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ ረገድ ኀብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን የገለፀው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሴቶች ለሰላም ፎረም በዛሬው ዕለት ባዘጋጀው የእግር ጉዞ መርሐ-ግብር ላይ ነው ።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ መንግሥትና ኅብረተሰቡ ሰላምን ለማስፈን ያልተቋረጠ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ሴቶች በሰላምና በግጭት አፈታት ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተሰራ መሆኑንም አስታውሰው ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እያከናወነ ላለው ስራ ምስጋና አቅርበዋል።

ሴቶች በመላው ኢትዮጵያ የሰላም ጥሪ እንዲያስተላልፉ የሴቶች ለሰላም የእግር ጉዞ መርሐግብር ማዘጋጀቱንም አመስግነዋል።

በቀጣይም ሰላምን በተመለከተ ለሚደረገው ጥረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ የእግር ጉዞው ዓላማ የተደረገውን የሰላም ስምምነት በማስመልከት ነው ብለዋል ።

በተለይም ሰላምን የሚያደፈርሱና ከሰላም ያፈነገጡትን ከማስቆም አንፃር ጉባኤው እየሰራ ያለውን ተግባር ለማሳየትና ለሰላም በመላው ኢትዮጵያ ጥሪ ለማቅረብ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም