የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን የተከተለ በ2 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን የተከተለ በ2 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያካሄደ ነው
ጎንደር፣ ታህሳስ 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን የተከተለ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ካህሌ ጀምበሬ ለኢዜአ እንደጠቆሙት፤ ዩኒቨርሲቲው በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በ4 ሺህ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ የበጋ መስኖ ልማት ስራውን እያካሄደ ነው፡፡
ለአርሶ አደሮቹ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴዎችን በስፋት ተግባራዊ እንዲሆኑ እየደገፈ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባቋቋማቸው አራት የምርምር የእርሻ ጣቢያዎች በመታግዝ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር የተላመዱ ምርታማ የስንዴ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተሻለ ግብዓትና ቴክኖሎጂ በመጠቀም እየለማ ካለው የስንዴ ሰብል 80 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ በበጋ መስኖ ልማቱ ለሚሳተፉ አርሶ አደሮች ከ4ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በማቅረብ እገዛ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
የአርሶ አደሩን ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ለመቀየርም ለስንዴ ልማቱ ሶስት የእርሻ ትራክተሮች የተገዙ ሲሆን አንድ የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነር ተገዝቶ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል፡፡
ባለፈው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ የስንዴ ልማት የተሳተፍነው ዩኒቨርሲቲው ባደረገልን የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ድጋፍ ነው ያሉት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መልካሙ ጀምበር ናቸው፡፡
ዘንድሮም በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ስንዴ እስከ 35 ኩንታል ስንዴ በማምረት ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በላይ ማሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ ከበሬ እርሻ ወደ ትራክተር እርሻ የሚያሸጋግረንን ቴክኖሎጂ በማምጣቱ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡
ለስንዴ ልማቱ ያዘጋጀሁት ግማሽ ሄክታር የስንዴ ማሳ በትራክተር ታርሶልኛል ያሉት አርሶ አደሩ በቀረበላቸው ማዳበሪያና ስንዴ ለመዝራት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ዞን በዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት ንቅናቄ 17ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 700 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ታውቋል፡፡