በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በቴክኖሎጂ በመከወን መረጃውን ለችግር መፍቻነት መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ

33

ባህርዳር፣ ታህሳስ 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በቴክኖሎጂ በመከወን የሚገኘውን ተጨባጭ መረጃ ለሁለንተናዊ ችግር መፍቻነት መጠቀም እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

የክልሉ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ምክር ቤት “በቴክኖሎጅ የዘመነ መረጃ በማበለጽግ የክልላችንን ከፍታ እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ ትናንት ምሽት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ተጨባጭ መረጃ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን ለመከወን ቁልፍ መሳሪያ ነው።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በአግባቡ በማከናወን መረጃውን ፖሊሲ ለመቅረጽ፣ የልማት እቅዶችን አቅዶ ለመተግበርና ፍትሃዊ የበጀት ድልድል ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዘመናዊ አስተዳደርን ለማስፈንና ትክክለኛ ፍትህ በመስጠት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉን ህዝብ ቁጥር፣ ስርጭቱንና ስብጥሩን በትክክል ማወቅ  በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን በየደረጃው ለማከናወን የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የወሳኝ ኩነት መረጃ ተቋምም ከወረቀት ስራ በመውጣት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተአማኒነት ያለው ምዝገባ ለማካሄድ በቁርጠኝነት መስራት አለበት ብለዋል።

በየደረጃው ያለው አመራር ለወሳኝ ኩነት ምዝገባ ትግበራ ልዩ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ ስራ እንዲያከናውን ርዕሰ መስተዳድሩ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት ዋና ሃላፊ ወይዘሪት መአዛ በዛብህ በበኩላቸው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማካሄድ ፍትሃዊ የልማት ስርጭት ለማስፈንና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በወሳኝ ኩነት ምዝገባ የተካተቱን የልደት፣ የሞት፣ የጋብቻ፣ ፍችና ጉዲፈቻ መረጃን በወቅቱ ሰንዶ መያዝ ለሚፈለገው አላማ ለማዋል የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከተጀመረበት ጀምሮ ባለፉት ስድስት ዓመታት ለመመዝገብ ከታቀደው 4 ሚሊዮን ኩነቶች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።

አፈጻጸሙም ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ብሎ የተገኘበት ሁኔታም በተፈጠረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝና አጋጥሞ በነበረው ጦርነት ስምንት ዞኖች ችግር ውስጥ በመቆየታቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

አገልግሎቱ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የኩነቶች ምዘገባ አፈጻጸምን 80 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

እቅዱን ለማሳካትም 60 በመቶ የሚሆነውን የምዝገባ አሰራር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አስደግፎ ለማከናወን የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በየደረጃው ያለው የከፍተኛ አመራር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ መስራት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የከተማ ከንቲባዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት መድረክም የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አስተዳደሮች እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም