ቀጥታ፡

በምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳይከሰት በመጀመሪያ ዙር የአምስት ሚሊዮን ኩንታል "ዩሪያ" ግዥ ተፈጽሟል

ታህሳስ 16/2015 (ኢዜአ) በዘንድሮው የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳይከሰት በመጀመሪያ ዙር የአምስት ሚሊዮን ኩንታል "ዩሪያ" ግዥ መፈጸሙን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ እንደገለጹት፤ በምግብ ራስን ለመቻል ከተያዘው አገራዊ ግብ አኳያ፤ ዘንድሮ አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ ሰብል ለመሸፈን ዕቅድ ተይዟል።

ምርታማነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ከሆኑ የግብርና ግብዓቶች መካከል የአፈር ማዳበሪያ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቅሰው፤ ለበጋ ስንዴ የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረበ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ እስካሁን በዘር ወቅት ጥቅም ላይ የሚውል 500 ሺህ ኩንታል "ኤን ፒ ኤስ" የአፈር ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች መተላለፋን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከባለፈው የምርት ዘመን የተረፉ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ እንዲሰራጭ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የዩሪያ ማዳበሪያ እጥረት እንዳይከሰት ግዥ መፈጸሙን ጠቁመው፤ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በመጀመሪያ ዙር የተገዛው 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ የማጓጓዝ ስራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመን የሚውል የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳይከሰት ከወዲሁ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም በተያዘው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ እያንዳንዳቸው 60 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ ሁለት መርከቦች ወደ ጅቡቲ እንደሚደርሱ ጠቁመዋል።

በተለይም አርሶ አደሩ በዘር ወቅት የሚጠቅምባቸው የአፈር ማዳበሪያ በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ በማጓጓዝ ለተጠቃሚዎች እንደሚከፋፈል ተናግረዋል።

የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ከዚህ አኳያ ለግብርናው ዘርፍ ስኬት ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም