ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል የሚገኙ ተጨማሪ 20 የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በጥቂት ቀናት ውስጥ ዳግም ስራ ይጀምራሉ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 16/2015 በትግራይ ክልል የፌደራል መንግስት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተጨማሪ 20 የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በጥቂት ቀናት ውስጥ ዳግም ስራ እንደሚጀምሩ የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።

ባንኩ መቀሌ ካለው ዲስትሪክት ጋር ተገናኝቶ የኦዲት ስራ ከተከናወነና ትክክለኛ ሂሳቡ ወደ ሲስተም ከገባ በኋላ ደንበኞች ገንዘብ ወጭ ማድረግ እንደሚፈቀድላቸውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በተቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች የተለያዩ ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ይታወቃል፡፡

ለአብነትም የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ የጤና ተቋማት፣ የባንክ አገልግሎት እንዲሁም ትምህርት ቤቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዳግም ስራ ጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ እንደተናገሩት ባንኩ በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር በሚገኙ የትግራይ ክልል ከተሞች የባንክ አገልግሎት የማስጀመር ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት 10 የሚደርሱ የባንኩ ቅርንጫፎች ዳግም አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ ተጨማሪ 20 የሚሆኑ የባንኩ ቅርንጫፎች ደግሞ በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል።

በሁሉም ቅርንጫፎች ዳግም አገልግሎት ለመጀመር የኤሌክትሪክ፣ስልክ እና ቅርንጫፎቹን ከዋናው መስሪያ ቤት ጋር ማገናኘት የሚያስችል የኢንተርኔት መሰረተ ልማቶች አስፈላጊ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ ከዋናው መስሪያ ቤት ጋር በሲስትም ያልተገናኙ የባንኩ ቅርንጫፎች አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን ገልጸው፤ ይህንን የማስተካከል ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት በተቆጣጠራቸው አንዳንድ አካባቢዎች በሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች ሰራተኞችን የማሟላት ስራ እየተከናወነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አገልግሎት አለመጀመሩንም አብራርተዋል፡፡

አገልግሎት መስጠት በጀመሩ ቅርንጫፎች ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ የሚላኩ ገንዘቦችን የመቀበል(ሃዋላ) እንዲሁም ገንዘብ የማስቀመጥ አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም አገልግሎት መስጠት በጀመሩ የባንኩ ቅርንጫፎች የደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም መቀሌ የሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች ከክልሉ ሌሎች አካባቢዎች ለመጡ ደንበኞች ጭምር ሲስተም ላይ ሳያስገቡ በማኑዋል አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ደንበኞች በባንኩ ያላቸው የሂሳብ መጠን ትክክለኛ መሆን አለመሆን ላይ ባንኩ እርግጠኛ መሆን ባለመቻሉ ገንዘብ ወጭ ማድረግ እንዳልተፈቀደ አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ባንኩ መቀሌ ካለው ዲስትሪክት ጋር ተገናኝቶ የኦዲት ስራ ከተከናወነና ትክክለኛ ሂሳቡ ወደ ሲስተም ከገባ በኋላ ደንበኞች ገንዘብ ወጭን ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ከመቀሌ ዲስትሪክት ጋር በሲስተም መገናኘት ሲጀምር በትግራይ ክልል ያሉ ቅርንጫፎቹን በሙሉ ዳግም አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም