ቀጥታ፡

ፖሊስ በትግራይ ክልል የሚገኙ የፌደራል ተቋማትንና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ (ኢዜአ ) ታህሳስ 16/2015 ፖሊስ መንግሥት በተቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ የፌደራል ተቋማትን እና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሸነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለፁ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቀጣናው የሚስተዋሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድም ተልዕኮውን በብቃት እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ በቀጣናዊና አገራዊ የፖሊስ አገልግሎት ጉዳዮች አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ሁለንተናዊ ሪፎርም ያደረገው የፌደራል ፖሊስ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ብቁ ቁመና እንዲኖረው አስችሎታል።

በትግራይ ክልል መንግስት በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ሰፊና የተቀናጀ የፖሊስ ኃይል በማሰማራት የፖሊሳዊ አገልግሎት ሚናውን በአግባቡ ሲወጣ መቆየቱን አውስተዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም በክልሉ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲሳለጥ፣ የሕክምናና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲከወኑ እና ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ፖሊስ ሰፊ ሥራ መሥራቱን ነው የተናገሩት።


በትግራይ ክልል የሚገኙ የፌደራል ተቋማት እና መሰረተ-ልማቶችን የመጠበቅ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑም አንስተዋል።


ኀብረተሰቡ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ በማድረግ፣ የገበያ ቦታዎችን ደኅንነት በማስጠበቅ፣ ባንክን ጨምሮ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ተቋማት ስራቸውን በአግባቡ እንዲያሳልጡ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


ለአብነትም በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው አክሱም ጺዮን ማርያም የንግስ በዓል በሰላም እንዲከበር ፖሊስ ትልቅ ኃላፊነት እንደተወጣ ጠቅሰዋል።


ከዚህ አኳያ የፌደራል ፖሊስ በክልሉ እየሰጠ ባለው ፖሊሳዊ አገልግሎት በሕብረተሰቡ ዘንድ ከተሰጠው ዕውቅና ባሻገር በዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ትልቅ አድናቆትና ምስጋና እንደተቸረውም ተናግረዋል።


በቀጣይም በክልሉ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚገኙ መሰረተ-ልማቶችን የመጠበቅ እና የሕዝቡን ደኅንነት የማረጋገጥ ሚናውን ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም