ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መረሃ-ግብር እንዲሳካ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል-ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩቱ

ባህር ዳር (ኢዜአ) ታህሣሥ 15/2015 የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር እንዲሳካ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ግብርና ሚኒስቴር፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ የአማራ ክልል ግብርና ምርምር እና ዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በመተባበር ያዘጋጁት የሌማት ቱሩፋት ላይ አውደ ጥናት ዛሬ  በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የኢንስቲትዩቱ መሪ ተመራማሪ ዶክተር ታደለ ደሴ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለሌማት ትሩፋት ያሳየው ቁርጠኝነት ሀገሪቱ ያላትን የእንስሳት ሃብት ምርታማነት ለማሳደግ የጎላ ድርሻ አለው።

ኢትዮጵያ በርካታ የእንስሳት ሃብት ያላት ሀገር ብትሆንም ከዚህ ቀደም ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ ከቁጥር ባለፈ በጥራትም ሆነ በመጠን ምርታማ በመሆን ረገድ ሰፊ ክፍተት እንደነበር ጠቁመዋል።

ይህም የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል ባለመቻሉ፣ በቂ የሆነ የመኖ አቅርቦትና የእንስሳት ጤና እንክብካቤ ችግሮች በመኖራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት መረሃ-ግብሩ ለእንስሳት ሃብት ምርታማነት ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ቀደም ሲል በስፋት ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች እንዲቃለሉ ያግዛል ብለዋል።

ለዚህም አለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስና አዳዲስ አሰራሮችን ተደራሽ በማድረግ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ሲሉ አስታውቀዋል።

የግብርና ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት በቁጥር ደረጃ በአፍሪካ 1ኛ እና ከዓለም ደግሞ 10ኛ እንደሆነች አውስተዋል።

ሆኖም ከእንስሳት ቁጥር ብዛት አንጻር ህዝቡ ተመጣጣኝ የሆኑ ወተት፣ ስጋ፣ እንቁላልና ማር የመሳሰሉ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ሰፊ ክፍተት እንዳለ አመልክተዋል።

ለዚህ ደግሞ በቂና ጥራት ያለው የመኖ አቅርቦት ከማቅረብ ጀምሮ ለእንስሳት ሃብቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ነው ብለዋል።

የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ለእንስሳት በቂ መኖ እንዲያገኙና የጤና እንክብካቤ እንዲሁም የእንስሳት ዝርያ ማሻሻልን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

''የሌማት ትሩፋት መረሃ-ግብር የምርምር ተቋማት የተሻለ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያፈልቁና እንዲያስተዋውቁ እድል የሚፈጥር ነው'' ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጥላየ ተክለወልድ ናቸው።

መረሃ-ግብሩ የምርምር ማዕከላት የእንስሳት ሃብትን ምርትና ማርታማነት ለማሳደግና የመኖ አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል የበለጠ ምርምር እንዲደረግ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የተለያዩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የፌዴራል፣ የክልል፣ ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላትና የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም