በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ብዝሃ ህይወት ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ ያለውን ህገ-ወጥ አደንና ሰፈራ ለመከላከል ድጋፍ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ብዝሃ ህይወት ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ ያለውን ህገ-ወጥ አደንና ሰፈራ ለመከላከል ድጋፍ ተጠየቀ

ጋምቤላ (ኢዜአ) ታህሳስ 15 ቀን 2015 በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ብዝሃ ህይወት ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ ያለውን ህገ-ወጥ አደንና ሰፈራ ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።
የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በብዝሃ ህይወት ሀብቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከታንዛንያው የሰረንገቲ ብሄራዊ ፓርክ ቀጥሎ በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፓርኩ ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ማሚቱ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በብሔራዊ ፓርኩ አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው ህገ-ወጥ አደንና ሰፈራ በብዝሃ ህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖበታል።
በአካባቢው እየተስፋፋ የመጣው ያልተገባ ኢንቨስትመንት ጭምር በፓርኩ ውስጥ በብዛት ይገኙ የነበሩትን የናይል ሊቾይ፣ የዝሆን፣ የቀጭኔ፣ የአንበሳና ሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳት ቁጥር እየተመናመነ ነው ብለዋል።

በተለይ በዝሆኖች ላይ ከፍተኛ የሆነ ህገ-ወጥ አደን እየተካሄደ ስለመሆኑ በቅርቡ ከጋምቤላ ወደ አዲስ አበባ ሲጓጓዝ በቁጥጥር ስር የዋለው የዝሆን ጥርስ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የፓርኩ ጽህፈት ባለፈው ዓመት ድንበር ዘለል አርብቶ አደሮች በርካታ የቀንድ ከብቶችን ወደ ፖርኩ ይዘው በመግባት ያደርሱት የነበረውን ጉዳት ከክልሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ ማስቆም መቻሉን አስረድተዋል።
በአሁን ወቅት በፓርኩ ላይ የሚደርሰውን ህገ-ወጥ አደንና ሰፈራ በማስቀረት ብዝሃ ህይወቱን ከጉዳት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩል የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የፓርኩ የዱር እንስሳት ረዳት ተመራማሪ አቶ ጌታሁን ገደፍ በበኩላቸው፤ የጋምቤላ ብሄራዊ ፓርክ በዱር እንስሳት ስርጭቱ ከታንዛንያው ከሰረንገቲ ብሄራዊ ፓርክ ቀጥሎ በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በፓርኩ እየተፈጸመ ባለው ህገ-ወጥ ሰፈራ፣ አደን፣ ደን ጭፍጨፋ ምክንያት ቀደም ሲል የነበረው የዱር የእንስሳት ቀንሷል ብለዋል።
ፓርኩ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጽህፈት ቤቱ ባለው ውስን የሰው ኃይል ብቻ ችግሩን ለመከላከል እንዳዳገተው ጠቁመው፤ ፓርኩን ከተደቀነበት አደጋ ለመታደግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

የጋምቤላ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኡቦንግ ኡቻላ ፤በፓርኩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ከጽህፈት ቤቱ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው በተለይም ህገ-ወጥ አደን የሚፈጽሙ አካላትን በመከታተል ለህግ ለማቅረብ ከፓርኩ ጽህፈት ቤትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።
ህገ-ወጥ ሰፋሪዎችንም ከፓርኩ ይዞታ እንደሚያስወጡም ጠቁመዋል።

በብሔራዊ ፓርኩ ብዝሃ ህይወት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመከላከል ከብሔራዊ ፓርኩ ጋር በመሆን ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጃክ ጂዮሴፍ ናቸው።

በበጀት ውስንነት ምክንያት በብዝሃ ህይወት ጥበቃ ዙሪያ ብዙ አልተሰራም ያሉት አቶ ጃክ፤ በቀጣይ ማህበረሰቡ ሀብቱን እንደራሱ ንብረት እንዲጠብቀው ግንዛቤ ለማፍጠር ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ 4 ሺህ 75 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ሲኖረው፤ በውስጡ 69 የአጥቢ ፣327 የአእዋፍ፣ የተሳቢ የእንሳሰትና 493 የዕጽዋት ዝርያዎች እንደሚገኙበት ከፓርኩ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።