ቀጥታ፡

ተመራቂዎች የሙያ ስነምግባር ተላብሰው ህዝባቸውን እንዲያገለገሉ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ መከሩ

ነቀምቴ ታህሣሥ 15/2015(ኢዜአ) ተመራቂዎች የሙያ ስነምግባር ተላብሰው ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ መከሩ።

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ  በአንደኛ ድግሪ፣ በሁለተኛ ድግሪና በሶስተኛ ድግሪ በተለያዩ ሙያ ያሰለጠናቸውን 811 ተማሪዎች ለ17 ዙር ዛሬ አስመርቋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት መመረቅ ህዝብን በሙያ ለማገልገል ዝግጁ መሆንን ያካትታል ሲሉ ተመራቂ ተማሪዎችም በተማሩራችሁበት ሙያ ስነምግባርን ጠብቃችሁ ያለአድልዎና አለባችሁ ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የእለቱ ተመራቂዎችም በተማሩት ሙያ ሕብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሜዳሌያ ተሸላሚ ተመራቂ ዶክተር ፍራኦል ኦልቀባ በሰጠው አስተያየት በተማረበት ሙያ ሕብረተሰቡን ሳያበላልጥ ለማገልግል ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለትምህርቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱም ለየሜዳሌያ ሽልማት ክብር መብቃቱን ተናግሮ ከኋላው ያሉት ተማሪዎችም የእሱን አርአያ ተከትለው ውጤት እንዲያመጡ መልእክቱን አስተላልፏል።

በአዋላጅ ነርስነት የዋንጫ ተሸላሚ ተመራቂ ዶክተር ዓለማየሁ ቶሌራ በበኩሉ ለትምህርቱ ትኩረት በመስጠት ባስመዘገበው ውጤት የዋንጫ ተሸላሚ በመሆኑ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል።

የጤናው ሙያ ዲሲፒሊን በሚያዘው መሠረት ሕብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀቱንም ዶክተር አለማየሁ አክለውም አመልክተዋል፡፡

በአራት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ቆይታው ለተደረገለት ድጋፍ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብና የወለጋን ህዝብ ያመሰገነው ደግሞ በህብረተሰብ ጤና የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ደቡብ ሱዳናዊው ጀምስ ቦል ነው።

ወደ አገሩ ደቡብ ሱዳን ሲመለስም በተማረው የሕክምና ሙያ ዜጎቹን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል 22 የሜዲካል ዶክተሮች፣ 41 የእንስሳት ጤና ዶክተሮች፣ 46 የጤና ኦፊሰሮች፣ 28 አዋላጅ ነርሶች፣ 89 የሜዲካል ላቦራቶሪ ባለሙያዎች፣ 83 ነርሶች፣ 45 የፋርማሲ ባለሙያዎች እንዲሁም 457 በተለያዩ ሙያዎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም