የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት የንባብ ባህልን ለማዳበር በትኩረት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት የንባብ ባህልን ለማዳበር በትኩረት እየሰራ ነው
ታህሳስ 15 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሕብረተሰቡን የንባብ ባህል ለማዳበር የመጻሕፍት ትርዒት በማዘጋጀት እንዲሁም መጻህፍትን በቅናሽ ዋጋ ለማኅበረሰቡ እንዲደርስ በማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት ገለጸ።
ለክልሎችና ዩኒቨርሲቲዎችም በቤተ-መጽሐፍት ሙያ፣ ሰነድና መዛግብት አስተዳደር ሥልጠናና ሙያዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።
በአገልግሎቱ የአብያተ-መጽሐፍት ዳይሬክተር ያሬድ ተፈራ እንደገለጹት፤ በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 27 የንባብ ክበባት ተቋቁመዋል።
ጎን ለጎንም በተለያዩ ጊዜያት የንባብ ሣምንት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የኅብረተሰቡን የንባብ ባህል ለማዳበር የመጻሕፍት ትርዒትና መጻህፍትን በቅናሽ ዋጋ ሽያጭ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቶች የንባብ ክበብ በመመሥረት የንባብ ልምድ በአንጋፋ ደራሲያንና ታዋቂ ሰዎች ሥልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል።
በማረሚያ ቤቶችም በቆይታቸው መጽሐፍ የጻፉ ደራሲያን በተለያየ ርዕሰ-ጉዳዮች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ መደረጉንም ጠቁመዋል።
ደራሲያን የንባብ ባህልን ለማሳደግ ያላቸውን ዕውቀት፣ ልምድና ክህሎት ለማኅበረሰቡ በአካል ቀርበው እያካፈሉ መሆናቸውን አቶ ያሬድ አስረድተዋል።
አገልግሎቱ መጻሕፍትን በመግዛት ቤተ-መጽሐፍትን የማደራጀት ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጓዳኝም በአገሪቱ የንባብ ባህል እንዲስፋፋ ለክልሎችና ዩኒቨርሲቲዎች በቤተ-መጽሐፍት ሙያ፣ በሰነድና በመዛግብት አስተዳደር በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት በመደበኛ መርሃ-ግብር ከ750 በላይ ባለሙያዎች ሥልጠናውን መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ከክልልና ከማዕከል ለተውጣጡ 24 ሰልጣኞች በሰነድና መዛግብት አስተዳደር የአሰልጣኞች ሥልጠና መስጠቱንም አመላክተዋል።
በክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ሥምምነቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።