በድንበር አካባቢ ያለውን ሰላም ለማስቀጠል ቀጠናውን በንግድ፣ በመንገድና በቱሪዝም ማስተሳሰር ይገባል-አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ - ኢዜአ አማርኛ
በድንበር አካባቢ ያለውን ሰላም ለማስቀጠል ቀጠናውን በንግድ፣ በመንገድና በቱሪዝም ማስተሳሰር ይገባል-አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
ጂንካ (ኢዜአ) ታህሳስ 15/2015 በአጎራባች ሀገራት ድንበር አካባቢ ያለውን ሰላም ለማስቀጠል ቀጠናውን በንግድ፣ በመንገድ መሰረተ ልማት እና በቱሪዝም እና በሌሎች ዘላቂ የልማት ስራዎች በማስተሳሰር ህዝቦችን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ሲሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተሳተፉበት የ"ኤኩሞሞር ፌስቲቫል" ኢትዮጵያ በውጭ ዲፕሎማሲዋ ለጀመረችው ቀጠናዊ ትስስር ስኬታማነት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተገልጿል።
"ኤኩሞሞር-ለቀጠናዊ ትስስር" በሚል መሪ ሀሳብ የኡጋንዳ፣ ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች የተሳተፉበት የባህል፣ የቱሪዝም እና የሰላም ፌስቲቫል በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ ካንጋቴን ከተማ ተካሂዷል።
በክብረ በዓሉ ላይ የታደሙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደገለጹት፣ የኤኩሞሞር ፌስቲቫል ዘላቂ ሰላምና ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር በኩል ሚናው የላቀ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በድንበር አካባቢ የታየው ሰላምና የህዝብ ለህዝብ ቅርርብ የኤኩሞሞር ፌስቲቫል ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።
የደቡብ ክልል ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርመሎ በበኩላቸው፣ የ"ኤኩሞሞር ፌስቲቫል" ኢትዮጵያ በውጭ ዲፕሎማሲ ለጀመረችው ቀጠናዊ ትስስር ስኬታማነት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ፌስቲቫሉ ካለው አዎንታዊ አበርክቶ አኳያ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በተሞክሮነት ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁመው፣ "በዓሉ እየሰፋ እንዲሄድ ክልሉ ድጋፉን ያጠናክራል" ብለዋል።
"ኤኩሞሞር የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ትስስር የሚያጠናክር እሴት ያለው ክብረ በዓል ነው" ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ናቸው።
ክብረ በዓሉ ጎልብቶ ለቀጠናው ትስስርና ለቱሪስት መስህብነት እንዲውል ብሎም ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን እንደመንግስት ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።
በድንበር አካባቢ የተገኘው ሰላም ከአጎራባች አገራት ህዝቦች ጋር በጋራ በመሆን የተሰራው ሥራ ውጤት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ናቸው።
አሁን ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው፣ በተለይም ቀጠናውን የሰላም፣ የልማት እና የቱሪዝም መስህብ ማዕከል ለማድረግ በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግስት ከጎረቤት አገራት መንግስታት ጋር በመሆን በድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦችን በንግድ እና በመንገድ መሠረተ-ልማት ለማስተሳሰር የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አስተዳዳሪው ጠይቀዋል።
"ኤኩሞሞር ለቀጠናዊ ትስስር'' በሚል መሪ ሀሳብ በተከበረው የሰላም ፌስቲቫል ላይ የክልልና የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች፣ ከምዕራብ ኢትዮጵያና ከደቡብ ክልል የመጡ የክብር እንግዶች በበዓሉ ላይ ታድመዋል።
በተጨማሪም ከአጎራባች አገራት ከኡጋንዳ-ካራሞጃንግ፣ ከኬኒያ-ቱርካና እና ከደቡብ ሱዳን-ቶፖሳና ጂዬ በመባል የሚጠሩና ከኛንጋቶም ማህበረሰብ ጋር ተመሳሳይ ቋንቋ ተጋሪ የሆኑና ተቀራራቢ ባህል ያላቸው ማህበረሰቦችና የቀጠናው አስተዳዳሪዎች ታድመዋል።
የኤኩሞሞር በዓል በቀጠናው ህዝቦች መካከል አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በድምቀት ተከብሯል።