ለገና እና ጥምቀት በዓላት ወደ አገራቸው የሚመጡ የዳያስፖራ አባላትን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለገና እና ጥምቀት በዓላት ወደ አገራቸው የሚመጡ የዳያስፖራ አባላትን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) 15/2015 የገና እና ጥምቀት በዓላትን ለማክበር ወደ አገራቸው የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
በ2014 ዓ.ም "ታላቁ ጉዞ ወደ አገር ቤት" እንዲሁም "ከዒድ እስከ ዒድ ወደ ሀገር ቤት" በሚል የተዘጋጀውን ጥሪ ተቀብለው በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ዳያስፖራዎቹ የገና እና ጥምቀት በዓላትን በአገራቸው ከማክበር ባሻገር በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውረው በመጎብኘት ለመልሶ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በ2014 ዓ.ም "ጉዞ ወደ አገር ቤት " በሚል የተጀመረው መርሃ-ግብር በየዓመቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት በሚከበረው የገና እና ጥምቀት በዓላት የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዓላቱን ለማክበር ወደ አገራቸው ለሚመጡ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎች አጋር አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የመሰረተ-ልማትና ሌሎች ቅድመ-ዝግጅቶች መደረጉን ጠቁመው፤ ሆቴሎችም እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች ላልይበላና አካባቢውን እንዲጎበኙ ፓኬጆች ተዘጋጅተዋል።
የሠላም ስምምነቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም መስህብ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች ለማስተዋወቅ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተዘጋጀው መርሃ-ግብር ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ መደረጉን ተናግረዋል።