ቀጥታ፡

ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ባለሀብቶች ጠየቁ

ሐዋሳ (ኢዜአ) ታህሳስ 15/2015 ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚደረገው ድጋፍ የኢኮኖሚ ሽግግሩን ከማፋጠን ባለፈ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ስለሚያስችል ሊጠናከር ይገባል ሲሉ በሲዳማ ክልል በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ጠየቁ፡፡

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በበኩሉ በዘርፉ የሚታየውን ማነቆ መፍታት የሚያስችል በጥናት የተገደፈ ሥራ መጀመሩን ገልጿል፡፡

ክልል አቀፍ 2ኛ ዙር "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ላይ የተገኙ ባለሃብቶች ለኢዜአ እንደገለጹት ሃገራዊ ንቅናቄው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ መነቃቃት ፈጥሯል፡፡

የአድማስ ተስፋ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለሁ አድማሱ እንዳሉት እንደሀገር የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሲዳማ ክልል በተለያየ ምክንያት ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ እድል ፈጥሯል፡፡

"አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ እንደሀገር የኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን የሚያፋጥንና ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል" ብለዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሃገር ውስጥ ለመተካትና እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ በመላክ ሂደት የኢንዱስትሪው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፣ ካላፈው ዓመት ጀምሮ የተሰጠው ትኩረትና የንቅናቄ ሥራው ሀገርና ባለሀብቱን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የ200 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚንቀሳቀስ የዱቄት ፋብሪካ ባለቤት የሆኑት አቶ አስቻለው፣ ፋብሪካው በቀጣይ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ወደ መገንባት እየተሸጋገረ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለኢንዱስትሪው መስፋፋት ሰላም ቀዳሚ መሆኑን ገልጸው" አሁን እንደሃገር የተጀመረው የሰላም ስምምነት መጠናከር ባለሀብቱን ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳና ዘርፉን የሚያሳድግ ነው" ብለዋል፡፡

የመስሪያ ቦታ፣ የብድር አቅርቦት፣ የውጭ ምንዛሬ እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶችን በተገቢው በማቅረብ ሂደት የመንግስት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሲዳማ ክልል ንግድና ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና በማኑፋክቼሪንግ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ መስፍን ቂጤሳ በበኩላቸው፣ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እየታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"እንደሀገር ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ በቅንጅት በተሰራው ሥራ የተገኘው ውጤት አመርቂ ቢሆንም ሲዳማ አዲስ ክልል በመሆኑ ያለውን የኢንዱስትሪ አቅም አሟጦ መጠቀም ይገባል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ተከትሎ ችግሮቻቸው ተፈቶላቸው ወደ ማምረት ሥራ የገቡ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም አሁንም የግብዓት እጥረቶች እንደሚስተዋል አመልክትዋል፡፡

ከማኑፋክቸሪንግ በተጨማሪ በቡና ምርት ላይ የተሰማሩት ባለሃብቱ ከ240 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል፡፡

የግብርና ምርቶችን ወደ ኢንዱስትሪ በማምጣት በኢኮኖሚው እደገት ላይ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሃዋሳ አግሪ ማኑፋክቸሪንግ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ደምሌ ናቸው፡፡

አቶ ዳዊት እንዳሉት በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የሃዋሳ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በመጀመሪያው ምዕራፍ የድንች ቺፕስ የማምረት ሥራ ጀምሯል።

በቀጣይም በሲዳማ ክልልና አጎራባች አካባቢዎች የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን ለማቀነባበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወሰደው ሃላፊነት ጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ኢንዱስትሪው ለሃገር እድገት የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ ንቀናቄው መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በበኩላቸው የኢንዱስትሪው ዘርፍ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ሚና ለማሳደግ በጥናት የተመሰረተ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ዘርፉ ቅንጅታዊ ድጋፍ ስለሚጠይቅ እንደ ክልል ሥራውን የሚያስተባብር አካል በማቋቋም ለኢንዱስትሪው ግብዓት የማሟላት ሥራ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር የአምስት ዓመት ስምምነት በመፈራረም ጥናትን መሰረት አድርገው የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል፡፡

ከግብዓት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በሲዳማ ክልል የሚገኙ ከ1ሺህ 50 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠራቸውም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም