ቀጥታ፡

ከዘንድሮው የመኽርና የመስኖ ስንዴ ልማት ከ107 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ

አዳማ (ኢዜአ) ታህሳስ 15/2015 በዘንድሮ ዓመት በመኽርና በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ከ107 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለፀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን በሀገር ደረጃ  በመኽር ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ተሸፍኖ በመሰብሰብ ላይ ነው።

በመኽር አዝመራ በስንዴ ከለማው መሬት ላይ ከ67 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ያሉት ዶክተር ማንደፍሮ፤ በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ካለው ምርት በሄክታር በአማካይ 31 ኩንታል እየተገኘ መሆኑን በማሳያነት አንስተዋል።

በተመሳሳይ በዚህ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በዘር ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ደግሞ 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በመኽር ከለማውና በመስኖ እየለማ ካለው ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ 107 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ነው ያሉት።

የምንጠብቀው ምርት የሀገራችንን የስንዴ ፍጆታ በበቂ ሁኔታ ይሸፍናል" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት የመኽሩን ሰብል ከመሰብሰብ ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሁሉም ክልሎች በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ጨምሮ ገልጸዋል።

በመስኩ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ በሀገርና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል መልካም ቁመና ላይ መገኘቱን ተናግረዋል።

ትርፍ ምርት በማምረት ለሀገር ውስጥ አግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች ከማቅረብ ባለፈ ስንዴን ወደ ውጭ በመላክ የሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እየሰራን ነው ብለዋል።

ሀገሪቷ  በየዓመቱ ከውጭ ስንዴ ለመግዛት ከ700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ታወጣ  ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ ባለፉት አራት ዓመታት በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

ይኸ የሚያሳየው በበጋ መስኖ ስንዴና በመኽር የስንዴ ልማት ላይ እየተከናወነ ያለው ስራ ትልቅ ውጤት እያመጣ ከመሆኑም ባሻገር የስንዴ ምርትና ምርታማነቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ ገልጸዋል።

ስንዴ ከምግብ ፍጆታነት አልፎ ለዓለም ገበያ በስፋት የሚቀርብበት ጊዜ ሩቅ እይደለም ያሉት ዶክተር ማንደፍሮ፤ ስንዴን ወደ ውጭ በማላክ የወጭ ምንዛሬ እናገኛለን ብለዋል።

ለዚህም አመች ሁኔታዎችና መፈጠራቸውን ጠቅሰው "የእኛ ስራ የሚሆነው ስንዴን በበጋና በመኽር በጥራትና በብዛት በእጥፍ ማሳደግ ነው"ብለዋል።

የአርሶ አደሩ የሜካናይዜሽን አገልግሎትና የውሃ አጠቃቀም፣ ምርጥ ዘርና የምርት ማሳደጊያ ግብዓቱን ጨምሮ የተሟላ ፓኬጅ አጠቃቀም እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ዶክተር ማንደፍሮ በበጋ ስንዴ ልማት የሜካናይዜሽን አገልግሎት እየተሻሻለ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም