የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ያስገነባው ዘመናዊ የፀሐይ ኃይል ምርቶች መፈተሻ ላቦራቶሪ ሥራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ያስገነባው ዘመናዊ የፀሐይ ኃይል ምርቶች መፈተሻ ላቦራቶሪ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 15/2015 የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የ250 ሺህ ዶላር ድጋፍ ያስገነባውን የፀሐይ ኃይል ምርቶች መፈተሻ ላቦራቶሪ ሥራ ጀመረ።
ላቦራቶሪው እስከ 350 ዋት የሚደርሱ የፀሐይ ኃይል ምርቶችን ለመፈተሽ የሚያስችል ነው ተብሏል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ እንደገለጹት፤ ከውጭ የሚገቡና በአገር ውስጥ የሚመረቱት የፀሐይ ኃይል አቅርቦትን ጥራት ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የ250 ሺህ ዶላር ድጋፍ ዘመናዊ የፀሐይ ኃይል ምርቶች መፈተሻ ላቦራቶሪ ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል።
ላቦራቶሪው በዋናነት ለገጠር ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚውሉ የፀሐይ ኃይል ምርቶችን የመፈተሽ፣ የመመርመርና የምስክር ወረቀት ለመስጠት እንደሚያስችልም ነው የገለጹት።
አገራዊ የጥራት ፖሊሲና የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ የላቦራቶሪው ግንባታ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

የድርጅቱ የኦፕሬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቤል አንበርብር በበኩላቸው፤ ላቦራቶሪው ውጤታማነትና ትክክለኛ ሪፖርት ማውጣት መጀመሩ በአፍሪካ ተጠቃሽ ያደርገዋል ብለዋል።
ድርጅቱ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ፍተሻ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
ምርቶች ኢትዮጵያ ያወጣቻቸውን አስገዳጅ መስፈርቶች ማሟላታቸውን የቅድመ ጭነት ፍተሻ በማድረግ በሚሰጡት ማረጋገጫ ምርቶቹ እንደሚገቡም አብራርተዋል።

ይህም የባለንብረቶችን ውጣ-ውረድ በመቀነስ ጥራት ያለው ምርት ወደ አገር እንዲገባ ያስችላል ብለዋል።
ድርጅቱ አሁን ላይ በዘመናዊ የፍተሻ ቴክኖሎጂዎች የተደራጁ ዘጠኝ የፍተሻ ላቦራቶሪዎች እንዳሉትም ተገልጿል።