ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የመጨረሻ የምርመራ ሪፖርት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የመጨረሻ የምርመራ ሪፖርት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ታህሳስ 14/2015 ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ወደ ኬንያ ናይሮቢ ሲበር ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የመጨረሻ የምርመራ ሪፖርት ይፋ ተደረገ።
አውሮፕላኑ ከቁጥጥር ውጪ ያደረገው ዋናው ምክንያት "ኤምካስ (MCAS)" የተባለው መቆጣጠሪያ በትክክል አለመስራቱ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡
የመጨረሻ ደረጃ የአደጋ ሪፖርትን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚንስትር ዳግማዊት ሞገስ ምርመራው ዓለም አቀፍ ሂደቶችን ተከትሎ መካሄዱን ገልጸዋል።
የምርመራ ቡድኑ ውስጥም አደጋው የደረሰበት ሀገር ባለሙያዎች፣ የአውሮፕላኑ አምራች ቦይንግ እና የአሜሪካ አቪዬሽን ባለሙያዎች መካተታቸውን እንዲሁም የፈረንሳይ እና የአውሮፓ አቪዬሽን በምርመራው እንዲሳተፉ መደረጉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በምርመራው መሰረትም የበረራ ባለሙያዎች በረራ ማድረግ የሚያስችላቸው ብቃትና ፈቃድ እንዳለቸው መረጋገጡን ገልጸው አውሮፕላኑ መብረር የሚያስችል የምስክር ወረቀት እንደነበረውም ገልጸዋል፡፡
አውሮፕላኑ ለበረራ ሲነሳ ትክክለኛ ክበደት መሸከም በሚያስችለው ሁኔታ ላይ እንደነበር መረጋገጡን ጠቁመዋል።
አውሮፕላኑ ከቁጥጥር ውጪ ያደረገው ዋናው ምክንያት "ኤምካስ (MCAS)" የተባለው ክፍል ከሲስተም ውጭ መሆኑን ነው የተናገሩት፡
ለምርመራ ስራው ስኬት ትብብር ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል፡፡