ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በ15ኛው ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ጉባኤ ላይ ለተደረሱ ውሳኔዎች የራሷን አስተዋጽኦ ማድረጓ ተገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 15/2015 ኢትዮጵያ በካናዳ ሞንቲሪያል በተካሄደው 15ኛው ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ጉባኤ ላይ ለተደረሱ ጠቃሚ ውሳኔዎች ድርድር በማድረግ የራሷን አስተዋጽኦ ማበርከቷን የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ከህዳር 28 እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2015 በካናዳ በተካሄደው 15ኛው ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የነበራትን ተሳትፎና የተላለፉ ውሳኔዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በጉባኤው የተሳተፈው የኢትዮጵያ ሉዕክ በዘላቂ ብዝሃ ህይወት ጥበቃና የተጎዱት መልሰው እንዲያገግሙ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የባለብዙና የሁለትዮሸ ውይይቶችን ማድረጉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በጉባኤው የአቅም ግንባታ፣ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ፣ የሃብት ማሰባሰብን ጨምሮ 35 የተለያዩ ውሳኔዎች መወሰናቸውን ገልጸዋል።

በብዝሃ ህይወት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስና ለማስቆም የዓለም አገራት ተባብረው መስራት የሚያስችላቸው የድህረ 2020 ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ማዕቀፍ ከጸደቁ ጉዳዮች ውስጥ ይገኝበታል።

በተደረጉ ውይይቶችና በጸደቁት ማዕቀፍና ስምምነቶች ላይ ኢትዮጵያ የራሷን እና የታዳጊ አገሮችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ሃሳቦችን በማንሳት ድርድር ማድረጓን ገልጸዋል።

በጉባኤው ብዝሃ ህይወታቸው ከተጎዳ የዓለም አካባቢዎች 30 በመቶ ወደነበረበት እንዲመለስ እንዲሁም 30 በመቶ የዓለም ክፍል በጥብቅ ክልልነት እንዲያዝም ከስምምነት ተደርሷል።

በብዝሃ ህይወት ሃብታቸው የበለጸጉ 20 አገራት ሃሳባቸውን በጋራ በማቅረብና ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ፈንድ እንዲቋቋም ጥያቄ በማቅረብ በኩል ኢትዮጵያ ትልቁን ድርሻ መውሰዷንም ጨምረዋል።

እንደ ዋና ዳሬክተሩ ገለጻ የበለጸጉ አገሮች የታዳጊ አገሮች በብዝሃ ህይወት ላይ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት በዓመት 200 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲያደርጉም ከስምምነት ተደርሷል።

በጉባኤ ላይ በተደረጉ ውሳኔዎች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ከፖሊሲ አውጭዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ይሰራል ተብሏል።

ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ጉባኤ በየሁለት ዓመቱ በብዝሃ ህይወት ጥበቃ፣ የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙና ያጋጠሙ ችግሮችን መከላከል ላይ አተኮሮ የሚመክር ነው።

ጉባኤው በዓለም አቀፉ የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ላለፉት አራት ዓመታት ሳይካሄድ መቆየቱም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም