አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለአፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዝግጅት ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለአፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዝግጅት ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ አደረጉ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 14/2015 አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለአፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዝግጅት ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ አደረጉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ሰባተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ዝግጅት ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል።
በአገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ከጥር 5 እስከ 27 2015 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 18 አገራት ይሳተፋሉ።
ዋልያዎቹ በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ አልጄርያ፣ ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር ተደልድለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዚህ ቀደም ለቻን ውድድር ቅድመ ዝግጅት 42 ተጫዋቾችን ያካተተ ጊዜያዊ የተጫዋቾች ጥሪ አድርገው እንደነበር ይታወሳል።
በድሬዳዋ እየተካሄደ በሚገኘው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ተገኝተው የተጫዋቾችን ወቅታዊ ብቃት እና ሁኔታ በመገምገም የተጫዋቾችን ቁጥር ወደ 28 በመቀነስ ጥሪ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ታህሳስ 18 ቀን 2015 ከቀኑ 5 ሰአት ጀምሮ በፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት በመገኘት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ተላልፏል።
ተጫዋቾቹ በቀጣዩ ቀን የጤና እና አካል ብቃት ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ልምምድ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።