የኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ማህበር በቤተሰብ ዕቅድ እና ጤና አጠባበቅ ላይ የሚተገበር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ማህበር በቤተሰብ ዕቅድ እና ጤና አጠባበቅ ላይ የሚተገበር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ
ታኅሳስ 14/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር በቤተሰብ ዕቅድ እና ጤና አጠባበቅ ላይ የሚተገበር የ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ኘሮጀክት ይፋ አድርጓል።
የማህበሩ ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ መኮንን እንደገለፁት፤ ኘሮጀክቱ በሶስት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን በርካታ እናቶችን የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከፖካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር እንደሚተገበርም ገልጸው ለፕሮጀክቱ ከተመደበው ወጪ ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚልዮን ዶላሩ ለቤተሰብ ዕቅድ ማስፋፋትና ጤና ጥራት አጠባበቅ ይውላል ብለዋል።
ግማሽ ሚሊዮን ያህሉ በሀገሪቱ በፀጥታ ችግር ምክንያት የጤና ሥርዓታቸው ለተዛባባቸው አካባቢዎች እገዛ እንደሚያገለግልም ነው ያነሱት፡፡
የፓካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ፕሮግራም ተጠሪ የምስራች በላይነህ ፤ፕሮጀክቱ በርካታ እናቶች የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።
ፋውንዴሽኑ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ግብአቶችን በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ጤና ኬላዎች እና የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ በሰሜኑ ግጭት ጉዳት የደርሰባቸውን ጤና ጣቢያዎች መልሶ በማቋቋም የህጻናት እና የእናቶችን ጤና ለማስጠበቅ እንዲሁም የባለሙያዎችን ስነ-ልቦና ለመገንባት የሚያግዙ ድጋፎች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡