በሽታን መቋቋም የሚችሉ የበርበሬ ዝርያዎችን በምርምር በማስፋት ለአርሶ አደሩ ለማድረስ እየተሰራ ነው-የሐዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል - ኢዜአ አማርኛ
በሽታን መቋቋም የሚችሉ የበርበሬ ዝርያዎችን በምርምር በማስፋት ለአርሶ አደሩ ለማድረስ እየተሰራ ነው-የሐዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታኅሳስ 14/2015 በሽታን መቋቋም የሚችሉ የበርበሬ ዝርያዎችን በምርምር በማስፋት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የሐዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በተለይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እንዲሁም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ መጠን ያለው በርበሬ ይመረታል፡፡
ምርቱ ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ለተለያዩ የፋብሪካ ምርቶች በግብዓትነት የሚያገልግል ሲሆን የበርበሬ ምርት ለበሽታ ካለው ተጋላጭነት አንጻር ለአርሶ አደሮች ትልቅ ፈተና መሆኑም ነው የሚገለጸው፡፡
በኢትዮጵያ የበርበሬ ምርት ላይ በስፋት ጥናትና ምርምር ከሚያደርጉ የግብርና ምርምር ማዕከላት አንዱ የሐዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል አንዱ ነው።

በማዕከሉ የሰብል ጥበቃ ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ሽፈራው መኮንን እንደሚሉት በኢትዮጵያ የበርበሬ ምርት ሽፋን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል።
ያም ሆኖ ሰብሉ በተደጋጋገሚ ለበሽታዎች ተጋላጭ መሆኑን ገልፀው፤ ማዕከሉም የበርበሬ ምርታማነትን ለመጨመርና በሽታ የሚቋቋም ዝርያ ለማፍለቅ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

የበርበሬ ምርታማነትን ለመጨመር በተለያዩ የአስተራርስ ዘዴዎችን በሰርቶ ማሳያዎች ላይ በመስራት ምርታማነትን ከነበረበት 18 ኩንታል ወደ 25 ኩንታል ማግኘት እንደተቻለ አንስተው በተመረጡ በርበሬ አብቃይ አካባቢዎች ላይ የዘር ብዜት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
የበርበሬ በሽታ የሚቋቋሙ ዝርያዎችን ለማፍለቅ ምርምሮችን እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ያም ሆኖ የበርበሬ ሰብል ምርምር ትልቅ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ ማዕከሉ የበጀት ውስንነት እንዳለበት ገልጸዋል።