በአፋር ስድስት ወረዳዎች በጦርነቱ የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር የጥገና ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ስድስት ወረዳዎች በጦርነቱ የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር የጥገና ሥራ እየተከናወነ ነው
ሰመራ (ኢዜአ) ታህሳስ 14/2015 በአፋር ክልል ቂልበቲ-ረሱ ዞን 6 ወረዳዎች በጦርነቱ የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር የጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አፋር ሪጅን አስታወቀ።
የሪጅኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሲን አሊ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በጦርነቱ ምክንያት በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ሀይል ለሁለት ዓመት በመቋረጡ ህብረተሰብ ለችግር ተዳርጎ ቆይቷል።
በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር የሚያስችሉ የጥገና ሥራዎች ከዋናው መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ያሲን እንዳሉት የጥገና ሥራዎቹ በዋናነት እየተከናወኑ ያሉት በራህሌ፣ ኩነባ፣ አበአላ፣ መጋሌ እና ዳሉል ወረዳዎች ነው።
ወረዳዎቹ ቀደም ሲል የኤሌክትሪክ ሃይል ሲያገኙ ከነበሩባቸው ንዑስ ጣቢያዎች ጋር መልሶ ለማገናኘት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እስከ አዋሳኝ ባሉ አካባቢዎች የገጠሙ የኤሌክትሪክ ብልሽቶችን ለመጠገን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የጥገና ሥራው እየተከናወነ ያለው በዋናው መስሪያ ቤት እና በሪጅኑ ባለሙያዎች ቡድን ነው።
በአሁኑ ወቅትም በአበአላ እና በራህሌ ወረዳዎች የጥገና ሥራው ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ጠቁመው፣ በኩነባ፣ መጋሌ እና ዳሉል ወረዳዎች የጥገና ሥራው በቀጣይ ሳምንት እንደሚጀመር አመልክተዋል።
የኤሌክትሪክ ሀይል ከተቋረጠባቸው ከሁለት ዓመት በላይ እንደሆናቸው የገለጹት ደግሞ የኩነባ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ መይረም መሀመድ ናቸው።
የሀይል መቋረጡ የሕክምናና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ እንቅፋት እንደሆነባቸውም ተናግረዋል።
አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ችግሮቻቸው ስለሚፈታ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ሥራው እንዲፋጠንላቸው ጠይቀዋል።
የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ መሀመድ አህመድ በበኩላቸው፣ በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት ለኑሮ ውድነትና መሰል ማህበራዊ ችግሮች ተጋልጠው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ችግሮቻቸውን እንደሚፈቱላቸው ጽኑ እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።