በጋምቤላ ክልል 60 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል 60 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ጋምቤላ (ኢዜአ) ታህሳስ 14 /2015 በጋምቤላ ክልል በበጋው ወራት 60 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከተተከሉ 10 ሚሊዮን ችግኞች መካከል 78 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውንም ቢሮው ገልጿል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮዊት ሉል ለኢዜአ እንደገለጹት በክረምቱ ወራት የነበረውን የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ በበጋው ወራት አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በበጋ ወራት በክረምቱ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብና ከሰደድ እሳት የመጠበቅ፣ በተራቆቱ አካባቢዎች የተጠናከረ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የተፋሰስ ልማት ስራውን ለማከናወን የባለሙያዎችንና የአርሶ አደሮችን አቅም የማጎልበት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተፈጥሮ የደን ሀብትም ሆነ አዲስ በተተከሉ ችግኞች ላይ የሰደድ እሳት ቃጠሎ እንዳይደርስ የመከላከያ መስመር ስራና በየቀበሌው የእሳት መከላከል ግብረ ኃይል የማቋቋም ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አጠቃቀም ዳሬክተር ኬት ቾል በበኩላቸው በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወራት በ100 ተፋሰሶች ውስጥ 60ሺህ ሄከታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ለማከናውን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በክልሉ ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ በ45 ቦታዎች ከተተከሉ 10 ሚሊዮን ችግኞች መካከል 78 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ተናግረዋል ።