ቀጥታ፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር ቱሪዝምን ማሳደግ የሚያስችል "ቪዚት ኢትዮጵያ" የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 14/2015 የቱሪዝም ሚኒስቴር ቱሪዝምን ለማሳደግ የሚያስችል "ቪዚት ኢትዮጵያ" የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያን ጨምሮ ሶስት አገልግሎቶችን ይፋ አደረገ።

ቱሪዝምን ለማሳደግና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት ያስችላል የተባለው የሞባይል መተግበሪያን ጨምሮ  የቱሪዝም ስማርት ካርድ አገልግሎትና ጉዞ የተሰኘ የንግድ ባንክ ልዩ የቁጠባ ሂሳብ አገልግሎት አይነት ነው።

ቪዚት ኢትዮጵያ የተሰኘው የሞባይል መተግበሪያ አምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችና አራት የውጭ ሀገር ቋንቋዎች የተካተቱበት ነው።

መተግበሪያው የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚያሰችል እንደሆነ ተገልጿል።

በዛሬው እለት ይፋ የሆነው ሌላው ጉዳይ የቱሪስት ስማርት ካርድ ሲሆን በተለይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የሆቴል ክፍያ፣ የመኪና ኪራይ እና ሌሎች ወጪዎችን በኦን ላይን ለመፈጸም የሚያስችል ነው።

ዛሬ ይፋ የሆነው ሶስተኛው ጉዳይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ለማበረታታት ጉዞ የተሰኘ የቁጠባ ሒሳብ አገልግሎት  ነው።

ይህ አገልግሎት ደንበኞች ለጉብኝት የሚሆን ቁጠባ የሚፈጽሙበት ሲሆን በግልም ሆነ በቡድን ለሚጠቀሙ ልዩ ማበረታቻ እንዳለው ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች  ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም