የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በወላይታ ሶዶ ከተማ ያስገነባውን የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ በዛሬው ዕለት አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በወላይታ ሶዶ ከተማ ያስገነባውን የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ በዛሬው ዕለት አስመረቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 14/2015 የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በወላይታ ሶዶ ከተማ ያስገነባውን የዳቦና ዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት ማስመቀሩን አስታወቀ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው መርቀው የከፈቱት የዳቦና ዱቄት ፋብሪካው በቀን 3መቶ ሺህ ዳቦ እና 42 ቶን ዱቄት በቀን እንደሚያመርት ተገልጿል፡፡

ፋብሪካው በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ሂቤይ ፒንግል ማሽነሪስ አጋርነት የተገነባ መሆኑ ተጠቅሷል።
የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ ጽህፈት ቤቱ በ11 ከተሞች ተመሳሳይ አቅም ያላቸው የዳቦና ዱቄት ፋብሪካዎችን በጋራ ለመገንባት ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ጋር ከተፈራረመ በኋላ ካስመረቃቸው መካከል ዛሬ ያስመረቀው አንዱ ነው::

ፅህፈት ቤቱ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በቀን 1 ሚሊየን እንዲሁም በአጋሮ ከተማ በቀን 3 መቶ ሺህ ዳቦ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን አስገንብቶ ማስመረቁ ይታወሳል::