የመንግስት ምስጢራዊ መረጃ ምደባና ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ እና የቴክኖሎጂ ዝግጁነት ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው

17

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 14/2015 የመንግስት ምስጢራዊ መረጃ ምደባና ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ እና የቴክኖሎጂ ዝግጁነት ላይ በአዲስ አበባ ውይይት እየተካሄደ ነው።

ረቂቅ አዋጁ የመንግስት መረጃዎችን ለመመደብ፣ ጥበቃ ለማድረግ፣ በየወቅቱ ለመፈተሽ እንዲቻልና ምስጢራዊ መረጃዎች እንዲጠበቁ እና እንዳይሰራጩ ለማስቻል የህግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የሚያስችል ነው ተብሏል።

በመድረኩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኙት አቶ ተስፋዬ ዳባ፤ ረቂቅ አዋጁ የአገር መረጃዎችን ለመመደብና ለመጠበቅ፣ መረጃዎቹ እንዳይጠፉ፣ እንዳይበላሹ አለበለዚያም ለሌላ አካል ተላልፈው እንዳይሰጡ ይረዳል ሲሉ አብራርተዋል።

ለዚህም የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው መረጃዎች ምስጢራዊነት ጠብቆ ለማቆየት ያግዛል ብለዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ፤ የአገር መረጃዎች ጥበቃ ካልተደረገላቸው በአገር እና ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ ብለዋል።

ለአብነትም ባለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቷ ያለችበት ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች መረጃዎች በተለያዩ ሁኔታዎች ሲወጡ መስተዋላቸውን ገልጸዋል።

መሰል አሰራሮችን መተግበር ሃገራዊ ምስጢርን በተለይም ወታደራዊ የግዥና ሌሎች የመረጃ ምስጢሮችንም ለመጠበቅ የሚስችል መሆኑን ነው የገለጹት።

አዋጁ ጸድቆ ተግባራዊ ሲደረግ ለአገራዊ መረጃዎች ጥብቅ ጥበቃና ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ውይይቱ ገንቢ ሃሳቦችን እና ግብአቶችን ለመሰብሰብ የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል።

አዋጁ የመረጃ ነጻነትን ባልገደበ መልኩ የአገር መረጃዎች ምስጢራዊነታቸው ተጠብቆ ለማስኬድ የሚረዳ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ይፈጥራል ተብሏል።

በመድረኩ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ፣ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም