በአማራ ክልል በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 250 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 75 ሺህ ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 250 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 75 ሺህ ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል
ደብረ ብርሀን (ኢዜአ) ታህሳስ 14/2015 በአማራ ክልል ዘንድሮው በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 250 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 75 ሺህ ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በሰሜን ሸዋ ዞን አንፆኪያ ገምዛ ወረዳ አገረማሪያም ሟጨራ ቀበሌ የክልል እና የዞን የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት የበጋ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሀይለማርያም ከፍያለው በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የበጋ ስንዴ ልማት 250 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በሁሉም ዞኖች በመኸር እርሻ ለምተው የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በማንሳትና ያሉ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በተደረገ ሁሉን አቀፍ ጥረት አስካሁን ድረስ 75 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
በመስኖ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ቴክኖሎጂዎች፣ የምርት ማሳደጊያ ግብአቶች እና ሌሎች ግብዓቶችን ፈጥኖ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በበኩላቸው፣ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ልማትን ለማፋጠን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ወቅቱ የበጋ መስኖ ልማት በስፋት የሚካሄድበት በመሆኑ አመራሩ አርሶ አደሩን በማነቃነቅ ያሉ የውሃ አማራጮችን ተጠቅሞ እንዲያመርት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
በየአካባቢው የሰላምና የልማት ሥራዎች እንዲሳለጡ ከማድረግ ባለፈ የህዝብን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
እንደሀገር ስንዴን በስፋት በማልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ ናቸው።
ለሀገራዊ ዕቅድ መሳካት ዞኑ የድርሻውን ለመወጣት በተያዘው በጋ 47 ሺህ 650 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በዘር ለመሸፈን አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን ጠቁመዋል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 80ሺህ 180 አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ የጠቆሙት ሃላፊው፣ "እስካሁን በተደረገ ርብርብ ቀድሞ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል" ብለዋል።
በበጋ የመስኖ ልማት ሥራ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ለገበያ ለማቅረብ መታቀዱንም አመልክተዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ስንዴን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ለመላክ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ክልሉ የበኩሉን ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ታውቋል።