ቀጥታ፡

የኤኩሞሞር ፌስቲቫል በኛንጋቶም ወረዳ ካንጋቴን ከተማ እየተካሄደ ነው

ካንጋቲን (ኢዜአ) ታህሳስ 14/2015 የኤኩሞሞር የቱሪዝም፣ የባህልና የሰላም ፌስቲቫል በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ ካንጋቴን ከተማ እየተካሄደ ነው።

በፌስቲቫሉ ላይ የኡጋንዳ፣ የደቡብ ሱዳን እና የኬኒያ አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑም ተገልጿል።

ፌስቲቫሉ "ኤኩሞሞር ለቀጠናዊ ትስስር" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

ፌስቲቫሉ "ኤኩሞሞር" የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን በኛንጋቶም ቋንቋ ''መሰባሰብ'' የሚል ትርጓሜ ያለው እንደሆነ ተመላክቷል።

ከኛንጋቶም ህዝብ ጋር የጠበቀ የባህል ትስስር ያላቸውና የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰቦች ከአጎራባች አገራት ተሰባስበው በጋራ የሚያከብሩት በዓል ነው።

ፌስቲቫሉ ኤኩሞሞር የሚል ስያሜ እንደተሰጠው የባህል አጥኚና የዞኑ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሎቱሮሲ ካሬ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ፌስቲቫሉ የሀገራቱ አጎራባች አርብቶ አደሮች ስለ ሰላማቸው የሚመክሩበት፣ ወንድማማችነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ይበልጥ  የሚያጎለብቱበት መድረክ መሆኑን በመጥቀስ።

በተጨማሪም ፌስቲቫሉ የባህል ትውውቅ የሚያደርጉበትና ትስስራቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩበት እንደሆነም አቶ ሎቱሩሲ ገልጸዋል።

በፌስቲቫሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ፣ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ተገኝተዋል።

እንዲሁም የክልሉ አርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ሎሬ ካኩታን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

ከኡጋንዳ-ካራሞጃንግ፣ ከኬኒያ-ቱርካና እና ከደቡብ ሱዳን-ቶፖሳና ጂዬ በመባል የሚጠሩ ከኛንጋቶም ህዝብ ጋር የአንድ ቋንቋና ባህል ተጋሪ የሆኑ ማህበረሰቦችና ከአጎራባች አገራት የቀጠናው አስተዳዳሪዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም