ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የቅድመ ወንጀል መከላከል ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የቅድመ ወንጀል መከላከል ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳሰ 13/2015 ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የቅድመ ወንጀል መከላከል ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አስገነዘቡ፡፡
የፖሊስና ህዝቡን ትብብርና የሚያጠናክር አገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድን በዛሬ እለት በይፋ ተመስርቷል፡፡
አማካሪ ቡድኑ ከፖሊስ ተቋማትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት ያሉበት ሲሆን የፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማሳለጥ የሚሰራ መሆኑ ተገልጿል።
የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከሲቪል ማህበራትና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አባላትን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።
ቡድኑ የወንጀል ስጋትን ለመቀነስና ቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም በማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ አማካሪ ቡድኑ የህብረተሰቡን ውክልና ይዞ የፖሊስ ተቋማትን የሚያማክር ገለልተኛ ቡድን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የቅድመ ወንጀል መከላከል ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ቡድኑ የወንጀል ስጋትን ቀድሞ በመለየት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ የአገልግሎት አሰጣጡን ውጤታማ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡
መንግስት ለአገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ተግባር ስኬቶች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የአማካሪ ቡድኑ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ በጸጥታ ማስከበር ሂደት ላይ ያሉ ስህተቶች እንዲታረሙ ይሰራል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የጸጥታ አካላትን ኑሮ መቀየር የሚችሉ ሃሳቦችንም በማመንጨት ተግባራዊ እንዲሆኑም ያደርጋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጋሹ አለማየሁ፤ አማካሪ ቡድኑ ከዚህ ቀደም የነበረውን የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት አደረጃጀቶችን ያጠናክራል ብለዋል፡፡
አገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በክልሎች ደረጃ ተቋቁሞ ውጤት ማስገኘቱ ተገልጿል።