ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እና የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳሰ 13/2015 የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እና የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርሰቲዎችን በመወከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተፈራርመዋል።

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ሥምምነቱ ኮሚሽኑ በክልል ዋና ከተሞች በሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ጽህፈት ቤቶችን ለመክፈት ያስችለዋል ብለዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ በአገሪቱ በሚገኙ 44 ዩኒቨርሲቲዎችና በሁሉም ካምፓሶቻቸው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን እንደሚያቋቁም ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ገለልተኛና ትንሿ ኢትዮጵያ ስለሚባሉ ጽህፈት ቤቶቹን ለመክፈት ኮሚሽኑ መወሰኑንም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተባብሮ መስራቱ የተቋቋመበትን ተልዕኮ ለመወጣት እንደሚያስችለው ተናግረዋል።

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ችግሮች ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ነው የጠቆሙት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምክክር መድረኩ አባል ሆኖ የሚፈለግበትን አስተዋጽኦ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ ኅብረተሰቡን በማወያየት፣ አዳራሽ በማመቻቸትና ባለሙያዎችን በማቅረብ እንደሚተባበሩም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም