የሲሚንቶ ፍላጎትና አቅርቦት እስከሚመጣጠን ድረስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ምርት የመሸጫ ዋጋ መንግስት ይተምናል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳሰ 13/2015 የሲሚንቶ ፍላጎትና አቅርቦት እስከሚመጣጠን ድረስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ምርት የመሸጫ ዋጋ መንግስት እንደሚተምን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ በሲሚንቶ መመሪያ ቁጥር 908/4014 አማካኝነት የሲሚንቶ ስርጭትና ግብይት ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በመረጧቸው አከፋፋዮች እንዲሆን ወስኖ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በወቅታዊ የሲሚንቶ ስርጭትና ግብይት ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተሻለ በልሁ በዚህ ወቅት እንዳሉት የሲሚንቶ ምርት ስርጭትን በተመለከተ የወጣው መመሪያ ቁጥር 908/4014 በአዲስ መመሪያ ተተክቷል፡፡

መመሪያ ቁጥር 908/4014 ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የሲሚንቶ ምርት አቅርቦት በ2013 በጀት ዓመት በአማካኝ ከሚመረተው 6 ነጥብ 1 ሚሊዬን ኩንታል በጥቅምት 2014 ወደ 4 ነጥብ 1 ሚሊዬን ኩንታል ዝቅ ብሏል ብለዋል፡፡

ሲሚንቶ በፋብሪካዎች መሸጫ ዋጋ እየቀረበ ቢሆንም ከመስከረም 5 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአግባቡ ሲሚንቶ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቁጥር ከሶስት አይበልጡም ብለዋል፡፡

በመሆኑም የሲሚንቶ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት በእጅጉ የሰፋ በመሆኑ አቅርቦቱ እስከሚስተካከል ድረስ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ በሚኒስቴሩ ተወስኖ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሰረት ፋብሪካዎች የትራንስፖርትና ትርፋቸውን ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ተመን በማውጣት ለመንግስት ያሳውቃሉ ብለዋል፡፡

የሲሚንቶ አምራቾች ለመረጧቸው አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪ ነጋዴዎች ምርት የሚያከፋፍሉ ሲሆን፤ አከፋፋዮቹ ከተቀመጠላቸው የዋጋ ተመን በላይ ሲሸጡ ካገኟቸው ውላቸውን አፍርሰው ለመንግስት ያሳውቃሉ ብለዋል፡፡

መንግስት የሲሚንቶ ምርቱ ግብይት በተቀመጠለት ዋጋና በደረሰኝ መከናወኑ የመቆጣጠርና የመከታተል ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡  

ለመንግስት ፕሮጀክቶች እና ለትላልቅ የግል አልሚዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ የተወሰነ ሲሆን፤ በዚህም እንደ አስፈላጊነቱ ከአከፋፋዮችም ሆነ ከቸርቻሪዎች መግዛት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ክልሎችና ዞኖች እጥረት እንዳይገጥማቸው ፋብሪካዎች ዋጋ ተምነው ተደራሽነታቸውን የሚያሳይ አሰራር መዘርጋት እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በኬላዎችና በተለያዩ ስፍራዎች የሲሚንቶ እንቅስቃሴን በመገደብና በማወክ በነፃ ግብይት ሂደቱ ላይ እንቅፋት መፍጠር እንዲሁም  ሲሚንቶን ለመቆጣጠር በሚል መውረስ የተከለከለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም