ቀጥታ፡

የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማነቆ በቅንጅት ለመፍታት እድል ፈጥሯል - ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

ሐዋሳ(ኢዜአ) ታህሳስ 13 ቀን 2015  የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ተቋማት ተቀናጅተው በዘርፉ ያለውን ማነቆ መፍታት የሚችሉበትን እድል በመፍጠሩ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

ክልል አቀፍ 2ኛ ዙር የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጠርበትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻልበት ቢሆንም ባለፉት ጊዜያት በቂ ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ባለፈው አመት የተጀመረው የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ዘርፉን በማነቃቃት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡

ዘርፉ ያለበትን ማነቆ ለመፍታት ተቋማት ተቀናጅተው መስራት የሚችሉበት ዕድል የፈጠረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤት እንዳመጣ ጠቁመዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት በተሰራው ስራ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በክልልና በፌደራል ባሉ ተቋማት ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲዎችና ከምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር ዘርፉን በሰው ሃይል የማደራጀት ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

የተገኙ ውጤቶች ጅምር በመሆናቸው ቀጣይነት ያለውን ስራ በማከናወን ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

ንቅናቄው ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚፈልግ የገለጹት ሚኒስትሩ የሲዳማ ክልልም ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የጀመረውን የአመራር ቁርጠኝነት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው በክልሉ ባለው ውስን የመሬት ሀብት ከፍተኛ ምርት በሚሰጡ ሰብሎችና እንስሳት እርባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ክልል ኢንዱስትሪ ላይ ማተኮር ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ ያለውን እድልና አቅም መለየት የሚያስችል በጥናት የተደገፈ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ማነቆዎች በትኩረት ከመደገፍ ባለፈ ለአዳዲሶቹ በተዘጋጀው ስትራቴጅክ እቅድ መሰረት ድጋፍ ለማድረግ የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በክልሉ በተከናወነው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች መለየታቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሬ ናቸው፡፡

ማምረት ካቆሙት መካከል ስምንቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው፤ 11 የሚሆኑት ደግሞ ችግሮቻቸው ተፈተው ወደ ማምረት ለመሸጋገር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ላለፉት ስምንት ዓመታት ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ የማምረቻና መሸጫ ቦታዎችን ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማጠናቀቅ ስራ እየተሰራ ሲሆን ሶስቱ ተጠናቀው ለኢንዱስትሪያሊስቶች ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉን የኢንደስትሪ አቅም ለይቶ ለማወቅና ለመምራት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ጥናት ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ተሰርቶ መጠናቀቁም ንቅናቄው የፈጠረው እድል ነው ብለዋል፡፡

 በክልሉ ያሉ ከ1 ሺህ በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል የማዕድ ብስኩት ፋብሪካ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሊያ በለጠ ኢንዱስትሪያቸው በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ በተፈጠረው እድል በ2014 ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ከ50 ሚሊዮን በሚበልጥ ካፒታል የሚንቀሳቀሰው ፋብሪካቸው በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የገበያ ትስስር ከመፍጠር ጀምሮ ባለሙያዎችን በማሰልጠንና በቦታው በመገኘት የማበረታታት ስራ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመድረኩ ባለፈው ዓመት በተከናወነው የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የተገኙ ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች የቀረቡ ሲሆን ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የኢንዱስትሪ ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም