ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት ቅነሳ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧን ጥናት አመለከተ

አዲስ አበባ  (ኢዜአ) ታህሳስ 13 ቀን 2015  ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አስርተ ዓመታት በእናቶች እና ጨቅላ ህጻናት ሞት ቅነሳ ከፍተኛ ማሻሻል ማስመዝገቧን አንድ ጥናት አመላክቷል፡፡

ጥናቱ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብር የተሰራ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ1990 እስከ 2020 ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው፡፡

በጥናቱ ይፋ ማድረጊያ ስነስርዓት ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር የጤና ቢሮ ተወካዮች፣ የልማት አጋሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ጤናና የስነ ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ ጌታቸው የጥናቱን ግኝት ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በእናቶች እና ጨቅላ ህጻናት ሞት ቅነሳ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።

በዚህም የእናቶችን ሞት በ61 በመቶ እንዲሁም የጨቅላ ህጻናትን ሞት በ55 በመቶ መቀነሷን ጠቅሰዋል፡፡

ውጤቱ የተመዘገበው እናቶች ከጽንሱ ጀምሮ የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ፣ በጤና ጣቢያ እንዲወልዱ፣ የጤና ግብዓቶች እንዲያሟሉ በመደረጉና የጨቅላ ህጻናት ስርዓተ ምግብ አተገባበር በመዘርጋቱ ነው ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት የተሻለ አፈፃፀም ማሳየቷን ጠቅሰው፤  የእናቶችና ህጻናት ጤና አጠባበቅ ላይ የጀመረችውን ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ፤ በቀጣይ የጨቅላ ህጻናትንና የእናቶችን ሞት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም