በቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚተገበር ዘላቂ የደን ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚተገበር ዘላቂ የደን ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2015 በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚተገበር ዘላቂ የደን ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
ፕሮጀክቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በደን የተሸፈነ መሬት ዘላቂነት ባለው መልኩ መጠበቅን አላማ ያደረገ ነው።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚሆነው ከስዊድን ኤምባሲ በተገኘ 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሆኑ ተነግሯል።
በፕሮጀክቱ በደን ጥበቃ ላይ የተሰማሩ አዳዲስና ነባር የጥበቃ አካላትን በማገዝ፣ የማህበረሰብ አቀፍ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻልና ለመደገፍ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ በአለም አቀፉ የአረንጓዴ እድገት ኢንስቲትዩት አማካኝነት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማቀፍ ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚተገበር መሆኑም ታውቋል።
የአለም አቀፉ የአረንጓዴ እድገት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ሃላፊ ዶክተር ገመዶ ዳሌ፤ ፕሮጀክቱ በክልሉ የደን ስነ ምህዳር ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅ ያስችላል ብለዋል።
የደን ሃብትን ለመጠበቅ በአካባቢው ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ማከናወን ግድ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም የተፈጥሮ ሀብቱ እንዲጠበቅ በማድረግ ግብርናውን በዘላቂነት ማሳደግ ይቻላል ብለዋል።
የክልሉ የደን የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ኢንጅነር አስራት ገብረማሪያም ፕሮጀክቱ በክልሉ ያለውን የደን ሀብት ለመጠበቅና በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር ይጠቅማል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ኅብረተሰቡን ስለ ደን አጠባበቅ ለማስተማርና ለማንቃት የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ በአካባቢው ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለመስራት ያግዛል ብለዋል።
የግሎባል አረንጓዴ ዕድገት ኢንስቲትዩት በደንና አካባቢ ጥበቃ የሚሰራ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።