የኤርትራ መንግስት በአገሪቷ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኤርትራ መንግስት በአገሪቷ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ጠየቀ
አዲስ አበባ መስከረም 20/2011 ኤርትራ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ከዘጠኝ ዓመት በፊት የተጣለባት ማዕቀበ እንዲነሳ ጠየቀች። የአገሪቷ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳላህ መሐመድ ጥያቄውን ያቀረቡት በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው "ምክር ቤቱ ከዘጠኝ ዓመት በፊት የጣለው ማዕቀብ የአገሪቷን ምጣኔ ሃብት ክፉኛ የጎዳ ከመሆኑም በላይ ዜጎችንም ለአላስፈላጊ መከራ ዳርጓል" ብለዋል። ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በቅራኔ ውስጥ በቆዩት ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከወራት በፊት እርቀ ሰላም መውረዱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል። የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀብ የጣለው ሶማሊያን ጨምሮ በጎረቤት አገሮች በሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች "እጇ አለበት" በሚል ነበር።