ባንኩ በሰጠው ብድር ለ140 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ በሰጠው ብድር ለ140 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል
አዲስ አበባ መስከረም 20/2011 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት አምስት ዓመታት በሰጠው የብድር አገልግሎት ለ140 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል። የባንኩ የእስትራቴጂ፣ ለውጥና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ሃይለየሱስ ለኢዜአ እንደተናገሩት አንድ የልማት ፕሮጀክት ሲቋቋም ፋይዳውን ከሚለኩ ነጥቦች አንዱ የፈጠረው የስራ እድል ነው። በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ባንኩ ከ39 ቢሊዮን ብር በላይ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ብድር የሰጠ ሲሆን፣ በዚህም 140 ሺህ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥረዋል። የተፈጠሩት የስራ እድሎችም በግብርና፣ ማእድንና በማምረቻ ዘርፍ ሲሆን ተሳትፏቸውም በሙያተኛና ጉልበት ሰራተኛ መሆናቸውን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ የሚቋቋሙ ፕሮጀክቶች የረጅም ጊዜ አትራፊነታቸው ከቀጠለም የተፈጠረው የስራ እድልም ቀጣይነት ያለውና እየሰፋ የሚሄድ ነው። ብድር የሚሰጠው የልማት ፕሮጀክት ከሚፈጥረው የስራ እድል በተጓዳኝ ሊያመጣ የሚችለው የውጭ ምንዛሬም ታሳቢ ይደረጋል። በመሆኑም ባንኩ ባለፉት አምስት ዓመታት ብድር ከሰጣቸው ተቋማት መካከል ለአብነት ከኤክስፖርት 66 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል። አንድ ፕሮጀክት በአገር ውስጥ ሲቋቋም ሊያስቀር የሚቸለው የውጭ ምንዛሬ፣ ለመንግስት የሚከፍለው ግብር፣ በአካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ፋይዳም እንዲሁ ብድር ለመስጠት ከግምት የሚገቡ ነጥቦች ናቸው። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ልዩ የፋይናንስ ተቋም ሲሆን የመንግስት የልማት አቅጣጫን መሰረት በማድረግ አዋጭ ለሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች ከአገር ውስጥና ከውጭ የብድር ገንዘብ በማሰባሰብ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጥ ነው። በባንኩ የፋይናንስ ድጋፍ የሚቋቃሙትን ፕሮጀክቶች እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ ለማድረግም ራዕይ አለው። ሆኖም እየጨመረ የመጣውን የገንዘብ ፍላጎት መሰረት በማድረግ እስትራቴጂክ እቅዱን በመከለስ ሂደት ላይ በመሆኑ ራዕዩም ከዚያ ጋር አብሮ ይከለሳል ብለዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ100 አመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ለፕሮጀክት ፋይናንስና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ይሰጣል። በመስኖ የሚለሙ ሰፋፊ የግል እርሻ ልማት ፕሮጀክቶች፣ የእርሻ ውጤቶች ማቀነባበሪያዎችና አምራች ፕሮጀክቶች የብድር አገልግሎት ከሚሰጣቸው ዘርፎች መካከል ናቸው። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያለበት አጠቃላይ ብድር ባለፉት 5 አመታት ከነበረበት 24 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በተጠናቀቀው በጀት አመት 70 ነጥብ 1 ቢሊዮን ደርሷል። የባንኩ አጠቃላይ ሃብት ደግሞ ባለፉት 5 አመታት ከነበረው 35 ቢሊዮን ብር በተጠናቀቀው 2010 በጀት አመት 78 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደርሷል።