ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሃን ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታኀሣሥ 12 /2015 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጠየቀ።

በአንድ አገር ሁለንተናዊ የዕድገትና የለውጥ ጉዞ ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ ቢሆንም በተቃራኒው ከሰሩ ደግሞ የውስብስብ ችግር ምክንያት መሆናቸው አይቀርም።

የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከጥፋት ይልቅ ልማትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርና መተሳሰብን እንዲሁም ሰላምን አጀንዳ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

በኢትዮጵያ የሚታዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን ለመፍታት የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሚናውን ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት የመገናኛ ብዙሃን ዋነኛ አጋዥ ሆነው እንዲሰሩ ጠይቋል።

ከመደበኛ የመገናኛ ብዙሃንና ከማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም አንቂዎች ጋር በዚሁ ዙሪያ ኮሚሽኑ በዛሬው እለት ምክክር አድርጓል።

የሀገራዊ ምክክር ጽንሰ ሀሳብ፣ ስለ ኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅና ስለ ሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነት ለባለሙያዎቹ ገለፃና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኘሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችና የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ሰፊ ግንዛቤ በመያዝ ለምክክሩ ስኬታማነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የተዛቡ መረጃዎችን አደገኛነት በመገንዘብ ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ አገራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚዲያ ሚና ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ በመጥቀስ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነርና የኮሚኒኬሽን ክፍል ሃላፊ ዶክተር ዮናስ አዳየ፤ የሚዲያ ባለሙያዎች በዘገባቸው የሀገራዊ ምክክሩን አስፈላጊነት የሚያጎሉ መረጃዎችን በማስተላለፍ ሰላማዊ ሀገር ለመፍጠር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የሀገር ግንባታ መሰረት የሚጠናከረው ከልማት ስራዎች ባለፈ በተደራጀ የመረጃና ኮሙንኬሽን ስራ የዘርፉ ባለሙያዎች በዚህ ዙሪያ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የድሬ-ቲዩብ ዋና አዘጋጅ ፍሬው አበበ፤ መገናኛ ብዙሃን ለምክክሩ ስኬታማነት ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዋ ሀና ረጋሳ፤ መድረኩ ለምክክሩ ስኬታማነት የሚረዱና ተዓማኒ የሆኑ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉ እንደሚያስችላቸው ጠቁማለች፡፡

ለኮሚሽኑ ስኬታማ ተግባር መገናኛ ብዙሃን ፣ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ ድጋፍ ሊያደረግ ይገባልም ብላለች።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1245/2014 መቋቋሙ ይታወሳል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም