የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ተግባራዊ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳራሻዎችን ለማስፋት የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ተግባራዊ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳራሻዎችን ለማስፋት የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 12/2015 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ተግባራዊ ሲሆን አህጉራዊ መዳረሻዎችን ለማስፋት የላቀ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስታወቀ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 አገሮች የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያን በሙከራ ደረጃ ለመጀመር በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው።
በዚህም የአፍሪካ አገሮች አየር መንገዶች አህጉራዊ በረራቸው ያለ ገደብ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ተግባራዊ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳራሻዎችን ለማስፋት ወሳኝ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
በተለይ በአየር ትራንስፖርትና አቪዬሽን ዘርፍ ሰፊ የገበያ ዕድል የሚፈጥር እንዲሁም በአፍሪካ ያለውን የበረራ ቁጥርና መስመሮች ለማስፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል ብለዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ተግባራዊነት ከአየር ትራንስፖርት ገቢራዊነት ጋር ተዳምሮ ለአየር መንገዱ ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጠርለት ገልጸዋል።
የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት በሀገሮች መካከል በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ምንም ዓይነት የትራፊክ ገደብ ሳይኖር መብረር ያስችላቸዋል ነው ያሉት አቶ መስፍን።
በአህጉሪቷ አንዳንድ ሀገሮች የበረራ ፈቃድ የማይሰጡ እንዳሉ አስታውሰው፤ መሰል ችግሮችን ለመፍታት የነጠላ ትራንስፖርት ዓይነተኛ መፍትሔ ይሆናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 39 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።