ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልእኮ መሳካት የምናደርገው አስታዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል- የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም - ኢዜአ አማርኛ
ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልእኮ መሳካት የምናደርገው አስታዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል- የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳሰ 12/2015 ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልእኮ መሳካት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም ገለጸ።
የማሰልጠኛ ተቋሙ በሰላምና ግጭት አፈታት የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ለመስጠት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት ተማሪዎችን ተቀብሏል፡፡
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከማላዊ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከሳውዲ አረቢያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኡጋንዳና ከሶማሊያ የተውጣጡ ዜጎች በስልጠናው ተካተዋል።
በሰልጣኞቹ የአቀባበል ስነ-ስርዓት በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ፍስሃ መኮንን እና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡
በመከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማሰከበር ማእከል ሃላፊ ሜጀር ጀኔራል አዳምነህ መንግስቴ፤ ተቋሙ በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታት የሚሰለጥኑ የተለያዩ አገራት ዜጎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው በ2014 ዓ.ም መሆኑን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ባለፉት አራት አመታት ካከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች ውስጥ ዘመኑን የሚመጥን ብቃት ያለው የሰው ሃይል ማፍራት አንዱ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
ተቋሙ ከዚህ በፊት አጫጭር ኮርሶችን ይሰጥ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ በአለም የሚታየው የሰላም ሁኔታ ውስብስብ መሆኑን ተከትሎ ለዚህ ምላሽ የሚሰጥ የሰው ሃይል ማፍራት በማስፈለጉ የትምህርት ክፍሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እንዲጀመር ተደርጓል ብለዋል፡፡
በስልጠናው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገራት በአለም አቀፍ ደረጃ ለሚያሰማሩት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ አጋዥ የሆነ የሰው ሃይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
"ከአገር የተሻገረ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ለማፍራት የምልመላ መስፈርቱን ማጠናከር በመቻላችን፣ የማስተማር አቅማችን አድጓል" ያሉት ሃላፊው ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልእኮ መሳካት የምናደርገው አስታዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ፣ አገራቸው ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ዘርፍ እያከናወነች ላለው ተግባር እውቅና እንደምትሰጥ ገልፀዋል፡፡
ጃፓን ዘርፉን ለመደገፍ በፋይናንስ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡
የተረጋጋች እና ሰላሟ የተረጋገጠ አፍሪካን እውን ለማድረግ ሰልጣኞቹ አደራ አለባቸው ያሉት አምባሳደር ኢቶ፣ መድረኩ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡
ፕሮግራሙ ሰልጣኞች የንድፈ ሃሳብና የተግባር እውቀት በመጨበጥ በአለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ፍስሃ መኮንን ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ስኬት ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የሚያደርገውን የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ1950 ዓ.ም አንስቶ በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥላ ስር ሰላም አስከባሪ ጦር በማሰማራት ከቀዳሚዎቹ አገራት አንዷ መሆኗን አውስተዋል፡፡