የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ መቆራረጥና መጥፋት በሥራችን ላይ ችግር ፈጥሯል--ነዋሪዎች እና ተቋማት - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ መቆራረጥና መጥፋት በሥራችን ላይ ችግር ፈጥሯል--ነዋሪዎች እና ተቋማት
ደሴ (ኢዜአ) ታህሳስ 12/2015 የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ መቆራረጥና መጥፋት በሥራቸው ላይ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን የደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች እና ተቋማት ገለጹ።
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደሴ ዲስትሪክት በበኩሉ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ የብረት ምሰሶና ገመድ ላይ የሚፈጸም ዝርፊያ ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት መሆኑን ተናግሯል።
በደሴ ከተማ በፀጉር ቤት ሥራ የሚተዳደረው ወጣት አቢ ሞላልኝ እንዳለው፣ ሰሞኑን የኤሌክትሪክ ሀይል በተደጋጋሚ መቆራረጥና አንዳንዴም ሙሉ በሙሉ መጥፋት በሥራው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።
በሀይል መቆራረጥ ምክንያት ሥራውን መስራት ባለመቻሉም የዕለት ገቢው በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የገለጸው ወጣቱ፣ በእዚህም የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም መቸገሩን ተናግሯል።
"በሂደት ለቤት ኪራይ የሚከፈል ገንዘብ ስለማጣ የሚመለከተው የመንግስት አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ቢሰጠን" ሲልም ጠይቋል።
በደሴ ከተማ የሕብረት ዳቦ ቤት ሥራ አስኪያጅ ሰይድ አብዱ በበኩሉ ከጓደኞቹ ጋር ተደራጅተው ዳቦ ቤት ቢከፍቱም፣ የኤሌክትሪክ ሀይል መጥፋትና መቆራረጥ ለኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑን ገልጿል።
በተለይ ሰሞኑን ችግሩ መባባሱ ሥራ እንዲፈቱ ከማድረግ ባለፈ የተቦካው ሊጥ በኤልክትሪክ ሀይል መቆራረጥ ምክንያት ተበላሽቶ ለመድፋት የተገደዱበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግሯል።
"የዳቦ መጋገሪያ ማሽናችንም አደጋ ላይ በመሆኑ ችግራችን ፈጥኖ ሊፈታልን ይገባል፤ ደንበኞቻችንም የችግሩ ተቋዳሽ ሆነዋል" ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ የሚኖረው ወጣት አፍወርቅ ደምስ በበኩሉ፣ ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በተጨማሪ የቤት ክዳን ቆርቆሮ ጭምር እየተሰረቀ መሆኑን አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎች ተደራጅተው በምሽት ጭምር አካባቢያቸውን መጠበቅ እንደጀመሩም ገልጿል።
የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሀይማኖት አየለ በበኩላቸው "የኤሌክትሪክ ኃይል በፈረቃ መሆኑ በሆስፒታሉ ሥራ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል" ብለዋል፡፡
ሥራችን ከሰው ሕይወት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ሆስፒታሉ ሀይል ለማግኘት ፈረቃ ውስጥ መግባት የለበትም ያሉት ሥራ አስኪያጇ፣ የሆስፒታሉ ጀኔሬትር መበላሸቱ ችግሩን እንዳባባሰው ጠቁመዋል።
በሆስፒታሉ በቀን እስከ 10 ሰው የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር አስታውሰው፣ "አሁን በኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት ሙሉ ለሙሉ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት አቋርጠናል" ብለዋል።
የድንገተኛና ሌሎች አነስተኛ ሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ቢሆንም፣ በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት ኮምፒውተር መጠቀም ባለመቻላቸው እየተቸገሩ በመሆኑ መንግስት ፈጣን መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደሴ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሀብቱ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት ከደሴ-ኮምበልቻ እና አካባቢው ያለው የኤሌክትሪክ መስመር በጦርነቱ ቢጎዳም ፈጣን ጥገና በማድረግ የሀይል አቅርቦት ማቅረብ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የተደራጁ ዘራፊዎች በብረት ምሰሶና እና ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ላይ ተደጋጋሚ ዝርፊያ በመፈጸማቸው በኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ችግር መፈጠሩን ተናግረዋል።
"ሰሞኑን በኮምቦልቻ ከተማ በአምስት የብረት ምሰሶዎች ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ በመፈጸሙ ከኮምቦልቻ-ደሴ-ወልድያ በሚሄደው የ66 ኪሎ ቮልት መስመር ላይ ችግር አጋጥሟል" ሲሉም ገልጸዋል።
ዘራፊዎቹ ምሰሶውን በመፍታትና ገመዱን ቆራርጠው በመውሰዳቸው ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ላይ ውድመት መድረሱን አቶ ሀብቱ አስረድተዋል።
በዚህም ለደሴ፣ ሐይቅ፣ ውጫሌ፣ ኩታ በር እና ሌሎች ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል በፈረቃ ለማቅረብ መገደዳቸውን ገልጸው፣ "በተወሰኑ ከተሞች ሃይል ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል" ብለዋል።
የተዘረፈውን የብረት ምሰሶ ለመተካት አዳጋች በመሆኑ የእንጨት ምሶሶ በመትከል ህብረተሰቡ ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ ቢደረግም በሀይል መጠንና ጥራት ላይ ጫና መፍጠሩን ጠቁመዋል።
የአካባቢው መስተዳድርና ህዝቡ ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ በኤሌክትሪክ ምሰሶና መስመሮች ላይ ዝርፊያ የሚፈጽሙ አካላትን ለህግ እንዲያቀርቡም አቶ ሀብቱ ጠይቀዋል።
በከተማው የስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደሥራ መግባቱን የተናገሩት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙህዬ ይማም ናቸው።
ወንጀለኞች ለጊዜው ቢሰወሩም ከህግ አያመልጡም ያሉት አቶ ሙህዬ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ ጭምር ስምሪት ተሰጥቶ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የደሴ ዲስትሪክት በምስራቅ አማራ ባሉ ዞኖች ከ400 ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳሉት ከዲስትሪክቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።