የባህል ስፖርቱን ማስቀጠል ባህልን ከማሳደግ ባለፈ መልካም ግንኙነትን ያጠናክራል - የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ - ኢዜአ አማርኛ
የባህል ስፖርቱን ማስቀጠል ባህልን ከማሳደግ ባለፈ መልካም ግንኙነትን ያጠናክራል - የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ
ጅማ ታህሳስ 12/2015 (ኢዜአ)የባህል ስፖርቱን ማስቀጠል ባህልን ከማሳደግ ባለፈ መልካም ግንኙነትን ያጠናክራል ሲሉ የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ የሱፍ ሻሮን ገለጹ።
ወረዳዎችን ያሳተፈ የጅማ ዞን የባህል ስፖርት ውድድር ዛሬ ተጀመረ።
ውድድሩ ባጠቃላይ በስምንት ዓይነት የባህል የስፖርት ዓይነቶች የሚደረግ ሲሆን ዓላማውም ባህልና የሰዎችን የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲያጠናክር ታስቦ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመክፈቻው መርሃ ግብር የተገኙት የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ የሱፍ ሻሮን እንዳሉት የባህል ስፖርት የዘመናዊዉ ስፖርት መሰረት እንደመሆኑ እንዳይረሳ በትኩረት ልንሰራበት ይገባል፡፡
የባህል ስፖርቱን ማስቀጠል በርካታ ማህበራዊ ጠቀሜታ እንዳለዉ የገለጹት አቶ የሱፍ፤ ባህልን ያሳድጋል መልካም ግንኙነትን ያጠናክራል ብለዋል፡፡
በለፉት አምስት አመታት በክልሉም ሆነ እንደ ጅማ ዞን ለባህል ስፖርት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነም አቶ የሱፍ አክለዋል፡፡
የጅማ ዞን ስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነጉማ መኮንን እንዳሉት ከሁሉም ወረዳዎች የመጡ የባህል ስፖርት ተወዳዳሪዎች ለቀጣይ 10 ቀናት ውድድሩን በመልካም ስነምግባር ታግዘው ያደርጋሉ፡፡
የባህል ስፖርት ተወዳዳሪዎቹ በስምንት የስፖርት አይነት እንደሚወዳሩ የገለጹት ሃላፊዉ ከነዚህ ውስጥ የትግል፣ የቀስት ውርወራ፣ የፈረስ ግልቢያ፣ የገና ጨዋታ እና ዝላይ ይገኙባቸዋል ብለዋል፡፡
በውድድሩ አሻናፊ የሆኑ ተወዳዳሪዎች ከጥር 2 ቀን 215ዓ.ም ጀምሮ በክልል ደረጃ ለሚደረገዉ የባህል ስፖርት ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ወጣት ጂቱ ዜኑ ከማና ወረዳ በትግል ባህላዊ ስፖርት ልትወዳደር መምጠቷን ገልጻ በውድድሩ እንደምታሸንፍ እምነቱ እንዳላት ተናገራለች፡፡
ሌላው የባህል ስፖርት ተወዳደሪ ወጣት ሀዊ ታጁ በበኩሏ በተለያዩ የባህል ስፖርት ለመወዳደር የመንቾ ወረዳን ወክላ መሳተፏን ተናግራለች፡፡