ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በሲሚንቶ ምርት እጥረት ምክንያት ለግንባታው ዘርፉ በቂ ግብአት ማቅረብ አሰቸጋሪ ሆኗል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 12/2015 በአዲስ አበባ በሲሚንቶ ምርት እጥረት ምክንያት ለግንባታው ዘርፉ በቂ ግብአት ለማቅረብ መቸገሩን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ገለጸ፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር በበኩሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከውጭ ምንዛሬና መለዋወጫ እቃዎች ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ችግሮች በመፍታት አቅርቦቱን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

በአዲስ አበባ በሲሚንቶ ምርት አቅርቦት እጥረት ሳቢያ በርካታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ ይገኛሉ።

የሲሚንቶ ምርት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅትና በንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በኩል ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ለከተማ አስተዳደሩ ቢወስንም እስካሁን ግን እጥረቱ እንደቀጠለ ነው ።

በመሆኑም የሲሚንቶ ምርት እጥረት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን እያዳከመና ለበርካታ ወጣቶችም የስራ አጥነት ምክንያት ሆኗል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ግርሻ ለኢዜአ እንደገጹት የሲሚንቶ ምርት አቅርቦትን በተያዘው እቅድ መሰረት ማከናወን አዳጋች ሆኗል።

በአምስት ወራት ጊዜ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ሲሚንቶ ለማከፋፈል ቢታቀድም ማሳካት የተቻለው 20 በመቶውን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከዳንጎቴ፣ ሙገር፣ ኢትዮ-ሲሚንት፣ ከደርባ እና ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርት በመረከብ ለደንበኞች የተሰራጨው ሲሚንቶ 384 ሺህ 500 ኩንታል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ 82 ሺህ 200 ኩንታል ለአምራች ማህበራት የተከፋፈለ መሆኑን ገልጸው ቀሪው ለግንባታው ዘርፍ ተዋንያን ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች በገቡት ውል መሰረት የሚጠበቅባቸውን ያክል ምርት ማቅረብ ባለመቻላቸው የአቅርቦትና ስርጭት እጥረቱ መከሰቱንም ገልጸዋል፡፡

በውጭ ምንዛሬ እጥረት መለዋወጫ ለመግዛት አለመቻል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብዓት ዋጋ መናርና የጸጥታ ችግር በቂ ምርት ማቅረብ አለመቻሉን ቢገልጹም ከፋብሪካዎች የወጣ 35 ሺህ 600 ኩንታል ሲሚንቶ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን ጠቁመዋል፡፡

ከአቅርቦት እጥረቱ ባሻገር ዳንጎቴ በ723 ብር፣ ሙገር በ788፣ ኢትዮ ሲሚንት በ761 ብር እንዲሸጡ ዋጋ ቢተመንላቸውም በህገ ወጥ መንገድ እስከ 2 ሺህ ብር በመሸጥ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ፋብሪካዎቹ እንዲያቀርቡ የተደረገው የማምረት አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ ቢሆንም እስካሁን ከቀረበው ምርት ውስጥ 262 ሺህ 400 ኩንታል የሚሆነው በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሲሚንቶ በሚከፋፈልባቸው አብነት፣ ጦር ኃይሎች፣ ኮልፌ፣ ቃሊቲ፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን፣ ጨው በረንዳና ቢስ ቅርንጫፎች እስከ 1 ሺህ 500 ሰዎች ተመዝግበው እስከ ሶስት ወር ወረፋ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር በበኩሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከውጭ ምንዛሬና መለዋወጫ እቃዎች ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ችግሮች በመፍታት አቅርቦቱን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ልማት ኢንስቲትዩት የሲሚንቶ እና ሌሎች ምርቶች ምርምር ዘርፍ ሃላፊ ስመኝ ደጉ፤ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በችግሮች ዙሪያ ተወያይተን የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡

የፋብሪካ ባለቤቶች የሚያነሷቸውን የውጭ ምንዛሬና ግብዓት እጥረት እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች በቅርቡ እልባት እንደሚያገኙ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

አዳዲስ የሲሚንቶ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ የኩዮና ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በጸጥታ፤ ኢስት-ሲሚንት ደግሞ በመለዋወጫ ችግር ምርት ማቆማቸውን በሳምንቱ በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሀገር ባለፉት አራት ወራት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ መመረቱን ገልጸው፤ ይሄውም ከማምረት አቅማቸው 72 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም መንግስት ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች በቂ የውጭ ምንዛሬ ለማቅረብና የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ህግ የማስከበር እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡

የንግድና ቀጣዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ቁምነገር እውነቱ የምርት ቁጥጥርና ስርጭቱን በተመለከተ መረጃ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም