ቀጥታ፡

የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ጥረት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 12/2015 በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚፈለገውን መዋቅራዊ  ሽግግር ለማምጣት በግብርናው ምርት ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ በማቅረብ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ይነገራል።

ኢትዮጵያ የቅመማቅመም ሰብሎችን ለማምረት ምቹ ስነ-ምህዳር ያላት ሲሆን ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማመንጨት እምቅ አቅም እንዳላትም እንዲሁ።

ካላት ሃብት፣ ስነ-ምህዳር ፣ የተመቻቸ የአየር ንብረትና የሰው ሃብት አንጻር ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም አለማግኘቷም ይገለጻለ።

በቅርቡም በመንግስት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይ የግብርና ምርቶችን ከጥሬው ይልቅ እሴት ጨምሮ መላክ ወቅቱ ለሚፈልገው ገበያ ተወዳዳሪነት እና ተጠቃሚነት ወሳኝ እንደሆነም በተለያዩ አካላት ሲገለጽ ይስተዋላል።

የላንድ ማርክ አግሮ ቢዝነስ የግል ድርጅት ባለቤት አቶ መክብብ ቶልቺሳ፤ በቅመማቅመም እና በመድኃኒት እጽዋቶችን በማልማትና እሴት ጨምሮ በመላክ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ይናገራሉ።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጠጅ ሳርን  በማልማት ወደ ውጭ ገበያ እየላኩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጠጅ ሳርን እሴት ጨምሮ ወደ ዘይትነት በመቀየርና  ለገበያ ለማቅረብ ሰፊ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

በቅርቡም የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ በመክፈት ምርቱ በብዛትና በጥራት እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑንም በመጠቆም።

ለመድኃኒትነት በብዛት ጥቅም ላይ ሲውል የሚስተዋለውን የጠጅሳርን ምርት እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ባለሃብቶችን ትርፋማ ከማድረግ ባለፈ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠንም ይረዳል ብለዋል።

ከጠጅሳር በተጨማሪም የጥብስ ቅጠል(ሮዝመሪ) መሰል መዓዛማ የቅመማቅመም ምርቶችን ማልማትና እሴት ጨምሮ አገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ዕቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አቶ መክብብ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አገሪቱ ከምርቱ ተጠቃሚ እንድትሆን 16 የቅመማቅመም ዓይነቶችን ለውጭ ገበያ  በማቅረብ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁሟል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እና ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ሻፊ ዑመር፤ ቅመማ ቅመም ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ ላይ  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ በጥሬው ከመላክ በቅመማቅመም ምርት ላይ እሴት ጨምሮ በመላክም ሆነ ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም