ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አርአያ ሊሆኑ ይገባል - የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል

ዲላ (ኢዜአ) ታህሳስ 12/2015 ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና ቅድሚያ በመስጠቱ ረገድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል ገለጸ።

ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን "አካታች የፈጠራ ስራና ሽግግራዊ መፍትሔ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት" በሚል መሪ ሐሳብ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች በዲላ ዩኒቨርሲቲ እየተከበረ ነው።

በስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ለጋሱ ልዑልሰገድ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ በሁሉም መስኮች ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት አየተሻሻሉ ናቸው።

ይሁንና ከጉዳት አልባዎች ጋር ሲነፃጸር አካል ጉዳተኞች ዛሬም ቢሆን በብዙ መንገድ የተገለሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ችግሩን ለማቃለልም ልማት ማዕከሉ ከመንግስትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አካል ጉዳተኞች እንደ ማንኛውም ዜጋ በሀገር ግንባታ እኩል ዕድል ሊያገኙ እንደሚገባ ጠቅሰው በዚህ ረገድ መንግስት ቀዳሚውን ኃላፊነት ሊይዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካል ጉዳተኞች የዕውቀትና ክህሎት ባለቤት አንዲሆኑ ስልጠና በመስጠት፣ አካታችነትን በማጠናከርና ምቹ መሰረተ ልማትና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍቃዱ ወልደማርያም በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ የመማሪያ ግብዓትን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁሶችን በማሟላቱ ረገድ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል።

ከመማር ማስተማር ስራዎች ጎን ለጎን በተለይም የህንጻ ግንባታዎች የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች አካታች እንዲሆኑ ከወረቀት ስራዎች ጀምሮ ልዩ ጥንቃቄ እየተደረገ እንደሚገኝ ለአብነት አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ከ162 በላይ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የልዩ ፍላጎት ትምህርትና ድጋፍ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አባቡ ተሾመ ናቸው።

ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ብሬል፣ የአካል ድጋፍና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ዩኒቨርሲቲው ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይም ከህንጻ ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል የካናዳ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዶክተር ታምሩ እውነቱ እንዳሉት በሀገር ውስጥና በውጭ ተስማሚ ቴክኖሎጂን ለዐይነ ስውራን በማስተዋወቅና በማቋቋሙ በኩል የተለያዩ ተግባራትን እያከነወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

አካል ጉዳተኞች በመማር ማስተማርም ሆነ በተመራማሪነት ብቁ ሆነው ወደ ተሻለ ሕይወት መሸጋገር እንዲችሉ በቴክኖሎጂ መታገዝ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግንባር ቀደም ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም