ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ በአባይ ተፋሰስ የልማት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ በአባይ ተፋሰስ የልማት እየተሰራ ነው
አዳማ (ኢዜአ) ታህሳስ 12/2015 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የአባይ ተፋሰስን ተከትሎ የተፋሰስ ልማት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለፀ።
በሚኒስቴሩ የውሃ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብረሃ አዱኛ ለኢዜአ እንደገለፁት የአባይ ተፋሰስ ለረዥም ጊዜ የእርሻ አገልግሎት ላይ የዋለና ተራራማ በመሆኑ አፈሩ በጎርፍ የሚጠረግበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።
ከአባይ ተፋሰስ ተጠርጎ የሚሄደው አፈር ደግሞ የታላቁ የህዳሴ ግድብን በደለል ሊሞላው ስለሚችል በተፋሰሱ ላይ ከወዲሁ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በዚህም ህዝቡን ያሳተፈ የተፋሰስ ልማት፣ የአፈርና ዕርከን ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በጥናትና ምርምር የተደገፈ የተፋሰስ ልማት፣ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ ዙሪያ ከዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።
አስካሁን ተፋሰሱን ተከትሎ የተሰራው ስራም ውጤት ማስገኘት መቻሉን የጠቀሱት ሚኒስትር ደኤታው በተፋሰስ ልማቱ ላይ ሁሉም ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በቅርቡም በኦሮሚያ ክልል አራት ቦታዎች፣ በአማራ ክልል ሶስት ቦታዎች እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሶስት ቦታዎች ተለይተው የተፋሰስ ልማት ስራ ይከናወናል ብለዋል።
''በተለይ በሳይንሳዊ ምርምር የታገዘ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትኩረታችን ነው'' ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ በአካባቢ ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ላይ ከሚሰሩ ሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዘንድሮው የበጋ ወራት የሚካሄድ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ሳይንሳዊ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ እንዲሁም ባለፈው ክረምት የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ ሁሉም የድርሻውን ማበርከት እንደሚገባ ጠቁመዋል።