ቀጥታ፡

ኪሊያን ምባፔ ከትንሿ ቦንዲ መንደር እስከ ዓለም ዋንጫ

የዓለም የእግር ኳስ ታላቅ ተጫዋችነትን ማዕረግ ከሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ተረካቢ የሚል አድናቆች እየጎረፉለት ያለው ፈረንሳያዊው ወጣት ኮከብ ኪሊያን ምባፔ ትናንት 24ኛ ዓመት ልደቱን አክብሯል።

ለመሆኑ ስለ ፈረንሳያዊው ፈጣን እና ጨራሽ አጥቂ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

. ኪሊያን ምባፔ ልክ የዛሬ 24 ዓመት እ.አ.አ ታህሳስ 20 ቀን 1998 በፓሪስ ከተማ ተወለደ።

. አባቱ ዊልፍሬድ ካሜሮናዊ የእግር ኳስ ተጫዋች እንዲሁም እናቱ ፋይዛ ላማሪ የአልጄሪያ የቀድሞ እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ነበረች።

. ምባፔ እግር ኳስን የጀመረው በስድስት ዓመቱ እ.አ.አ ከ2004 አባቱ ዊልፍሬድ በሚያሰልጥኑ ኤኤስ ቦንዲ በተሰኘ ክለብ ነው።

. “ለመጀመሪያ ጊዜ ሳሰለጥነው እድሜው ስድስት ነበር ከሌሎቹ የተለየ እንደነበር ያስታውቃል፤ ኳስን የሚያንከባልልበት መንገድ በጣም አስደናቂ ከሌሎቹ አንጻር ያለው ፍጥነት የሚያስደንቅ ነበር። በ15 ዓመት የአሰልጣኝነት ቆይታዬ እንደሱ ዓይነት ምርጥ ተጫዋች በፍጹም አይቼ አላውቅም በቃ እሱ ምርጥ ነው” ሲሉ በወቅቱ የፈረንሳዩ ክለብ የታዳጊ ቡድን አሰልጣኞች አንዱ የነበሩት አንቶኒዮ ሪካርዲ በአንድ ወቅት በሰጡት አስተያያት ገልጸዋል።

. ምባፔ ከቦንዲ ክለብ በኋላ ወደ ታዋቂው የፈረንሳይ የእግር ኳስ አካዳሚ ክሌርፎንቴን አመራ፤ በአካዳሚው ያሳየው አስደናቂ ብቃት በታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች አይን ውስጥ እንዲገባ አደረገው።

.በርካታ የፈረንሳይ ክለቦችን ጨምሮ ማንችስተር ሲቲ፣ሪያል ማድሪድ፣ሊቨርፑል፣ ቼልሲ እና ባየር ሙኑክ ተጫዋቹን ለማስፈረም ሙከራ አደረጉ።

.የስፔን ታላቅ ክለብ ሪያል ማድሪድ ምባፔ የ11 ዓመት ታዳጊ እያለ ከክለቡ ከ12 ዓመት በታች ቡድን እንዲለማመድ እና የክለቡን የስፖርት ፋሲሊቲዎች እንዲጎበኝ አደረገ።

. ከሶስት ዓመት ቆይታ በኋላ በ14 ዓመቱ ቼልሲ ባደረገለት ግብዣ ወደ ለንደን በመምራት የክለቡ ወጣት ቡድን ከቻርልተን አትሌቲክ ጋር ባደረገው ጨዋታ ተሰልፏል።

. ይሁንና የብዙ የአውሮፓ ክለቦች አይን ያረፈበት ኪሊያን ምባፔ ወደ ፈረንሳይ በመመለስ ለሞናኮ መጫወት ጀመረ። ሞኖኮ ለአጥቂው የእግር ካስ እድገት መሰረት የጣለ እንደሆነም ይነገራል።

. እ.አ.አ ታህሳስ 14 ቀን 2016 ሞኖኮ ሬንስን በፈረንሳይ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ 7 ለ 0 በረታበት ጨዋታ በማስቆጠር በእግር ካስ ቆይታዊ የመጀመሪያ ሀትሪኩን ሰራ።

.ምባፔ እ.አ.አ የካቲት 11 ቀን 2017 ሞናኮ በፈረንሳይ ሊግ 1 ሜትዝን 5 ለ 0 ሲረታ ሀትሪክ የሰራ ሲሆን ሶስቱን ግቦችን ሲያገባ አድሜው 18 ዓመት ከ 2 ወር ነበር። ይሄም በሊጉ ከሌላኛው ፈረንሳዊ ተጫዋች ጀርሚ ሜኔዝ በመቀጠል ሀትሪክ የሰራ ወጣት ተጫዋች መሆን ችሏል።

.በፈረንሳይ ሊግ 1 የመጀመሪያ ሀትሪኩን ካስቆጠረ ከአራት ቀናት በኋላ በኢቲሃድ ስታዲየም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሞናኮ 5 ለ 3 ሲሸነፍ ግብ አስቆጠረ። ይህም ከካሪም ቤንዚማ በመቀጠል በአውሮፓ ውድድሮች ግብ ያስቆጠረ ሁለተኛው ወጣት ተጫዋች እንዲሆን አድርጎታል።

.ሞናኮ እ.አ.አ በ2016/17 የውድድር ዓመት ከ16 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ የፈረንሳይ ሊግ 1 ዋንጫን ሲያነሳ 15 ግቦችን አስቆጥሯል። በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ በ46 ጨዋታዎች 28 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

.ሞናኮ እ.አ.አ በ2016/17 የውድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በጣልያኑ ጁቬንቱስ በግማሽ ፍጻሜው በድምር ውጤት 4 ለ 1 ተሸንፎ እስከተሰናበት ጨዋታ ድረስ በውድድሩ ላይ አስደናቂ ብቃት አሳይቷል። ስድስት ግቦችን በሻምፒዮንስ ሊጉ ማስቆጠር ችሏል።

.የፈረንሳዩ ክለብ ፓሪሰን ጀርሜን እ.አ.አ በ2017/18 ዓመቱን ወጣት አጥቂ ኪሊያን ምባፔን በ180 ሚሊዮን ዩሮ በከፍተኛ የዘውውር ዋጋ ከሞናኮ አስፈርሞታል። 29 ቁጥር ማልያ ተሰጠው።

.የዝውውር ዋጋው ከኔይማር በመቀጠል የዓለማችን ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት ተጫዋች እንዲሆን አድርጎታል።

.ምባፔ እ.አ.አ በ2017/2018 የውድድር ዓመት ለፒኤስጂ በፈረንሳይ ሊግ አንድ 28 ጨዋታዎችን አደርጎ 13 ግቦችን አስቆጠረ። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም በስምንት ጨዋታ አራት ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ በሁሉም የውድድር አይነቶች 46 ጨዋታዎችን አድርጎ 21 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

.ምባፔ እ.አ.አ ታህሳስ 6 /2017 ፒኤስጂ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በባየር ሙኒክ 3 ለ 1 ሲሸነፍ ግቧን ሲያስቆጥር እድሜው 18 ዓመት ከ11 ወር ነበር። ይሄም በሻምፒዮንስ ሊጉ በወጣት እድሜው 10 ጎሎችን ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች አድርጎታል።

.ፈረንሳዊው ተጫዋች ከፒኤስጂ ጋር እ.አ.አ 2017/18 የውድድር ዓመት የፈረንሳይ ሊግ 1 እና የፈረንሳይ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን አንስቷል።

.ኪሊያን ምባፔ እ.አ.አ በ2018/19 የውድድር ዓመት ብራዚላዊው ሉካስ ሞራ ክለቡን ሲለቅ ይለብስ የነበረውን ሰባት ቁጥር ማልያ አድርጎ መጫወት ጀመረ።

.ምባፔ በውድድር ዓመቱ 33 ግቦችን በማስቆጠር የፈረንሳይ ሊግ 1 ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቀቀ። በሊጉ ባሳየው አስደናቂ ብቃት የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በ8 ጨዋታ 4 ግቦችን አስቆጠረ። በአጠቃላይ እ.አ.አ በ2018/19 ለፒኤስጂ በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው 43 ጨዋታዎች 39 ግቦችን አስቆጥሯል።

.እ.አ.አ ጥር 20/2018 ፒኤስጂ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የቤልጂየሙን ክለብ ብሩጅ 5 ለ 0 ሲረታ ምባፔ ሀትሪክ ሰርቷል። ሀትሪክ ሲሰራ አድሜው 20 ዓመት ከ 306 ቀን የነበረ ሲሆን ይሄም በወጣት እድሜው በሻምፒዮንስ ሊግ 15 ግቦችን ያስቆጠረ የመጀመሪያ ተጫዋች እንዲሆን አድርጎታል።

.ኪሊያን ምባፔ እ.አ.አ በ2019/20 የውድድር ዓመት አስደናቂ ግስጋሴውን በመቀጠል በ20 ጨዋታዎች 18 ግቦችን በማስቆጠር ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት የፈረንሳይ ሊግ 1 ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቀቀ። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በ10 ጨዋታ 5 ግቦች ከመረብ ላይ አሳረፈ። በውድድር ዓመቱ በሁሉም አይነት ውድድሮች በ37 ጨዋታዎች 30 ግቦችን ማስቆጠር ቻለ።

.ኪሊያን ምፓቤ በኮቪድ 19 በመያዙ ምክንያት እ.አ.አ 2020/21 በፈረንሳይ ሊግ 1 ፒኤስጂ ያደረጋቸውን የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ አልቻለም ነበር። ይሁን እንጂ በውድድር ዓመቱ በ31 ጨዋታዎች 27 ግቦችን በማስቆጠር በአስደናቂ ሁኔታ ለሶስተኛ ተከታታይ የዓመት የሊጉ ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቀቀ። እ.አ.አ ታህሳስ 5 ቀን 2020 ሞንፔሊዬ ላይ በሊጉ ያስቆጠራት ግብ በፒኤስጂ ማልያ ያስቆጠራት 100ኛ ገብ ሆና ተመዝግባለች።

.በውድድር ዓመቱ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 20 ግቦችን በወጣት እድሜው ያስቆጠረ ተጫዋች የሚል አዲስ ታሪክ ቢሰራም ክብረ ወሰኑ በዛው ዓመት ለቦሪሲያ ዶርትሞንድ ይጫወት በነበረው ኖርዌያዊ አጥቂ አርሊንግ ሃላንድ ተሰብሯል።(ሃላንድ በአሁኑ ሰአት የእንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ ተጫዋች ነው)

. እ.አ.አ የካቲት 16/2021 በካምፕ ኑ ስታዲየም ፓሪሰን ጀርሜን ባርሴሎናን 4 ለ 1 ሲያሸንፍ ሀትሪክ የሰራ ሲሆን ይህም ከዬጅሬናዊው አንድሬ ሼቭቼንኮ እና ከኮሎምቢያዊው ፋውስቲኖ አስፕሪላ በመቀጠል በሻምፒዮንስ ሊጉ በስፔኑ ክለብ ላይ ሀትሪክ የሰራ ሶስተኛ ተጫዋች አድርጎታል።

.ምባፔ በውድድር ዓመቱ የፈረንሳይ ሊግ 1 አሸናፊ መሆን ባይችልም የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠ ሲሆን የዓመቱ የሊጉ ምርጥ 11 ስብስብ ውስጥ ተካቷል።

.እ.አ.አ 2021/22 ኪሊያን ምባፔ በ35 ጨዋታዎች 25 ግቦችን በማስቆጠር ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት የፈረንሳይ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ታሪክ መስራት ቻለ።

.ምባፔ እ.አ.አ ታህሳስ 12/2021 በፈረንሳይ ሊግ 1 በቀድሞ ክለቡ ላይ ሁለት ግቦችን በማሳረፍ በፈረንሳይ ሊግ 1 ለፒኤስጂ ያስቆጠራቸውን ግቦች 100 አደረሰ። ሞናኮ ላይ ግብ ሲያስቆጥር እድሜው 22 ዓመት ከ357 ቀናት ነበር። ይህም የብሪታኒያው የስፖርት ትንተና ኩባንያ እግር ኳስ መረጃዎችን መመዝገብ ከጀመረበት ከእ.አ.አ 1950/51 አንስቶ በፈረንሳይ ሊግ ለአንድ ቡድን 100 ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች አድርጎታል።

.በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በ8 ጨዋታ ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳረፈ። በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ በ46 ጨዋታዎች 39 ግቦችን በማስቆጠር አስደናቂ ግስጋሴውን ቀጠለ።

.ምባፔ እ.አ.አ ግንቦት 21/ 2022 በፒኤስጂ እስከ 2025 መቆየት የሚያስችለውን ስምምነት በመፈራረም ውሉን አስረዘመ። በወቅቱ ፈረንሳዊው ተጫዋች ወደ ስፔኑ ክለብ ያመራል የሚሉ ዘገባዎች በስፋት ሲወጡ ነበር። ምባፔ በአዲሱ ውሉ በወር አራት ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ያገኛል።

.ኪሊያን ምባፔ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በፈረንሳይ ሊግ 1 በ14 ጨዋታዎች 12 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በመምራት ላይ ነው። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ በስድስት ጨዋታ ሰባት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን በ20 ጨዋታዎች 19 ጎሎችን ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

.ምባፔ ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው እ.አ.አ መጋቢት 25 /2017 ፈረንሳይ ሉክሰምበርግን 3 ለ 1 ባሸነፈችበት የ21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ነበር። በ78ኛው ደቂቃ ዲሚትሪ ፓዬትን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል። እድሜውም 18 ዓመት ከ 3 ወር ከ5 ቀናት ነበር። ይሄም ከማርያን ዊስኔውስኪ በመቀጠል በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የተሰለፈ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች አድርጎታል። ዊስኔውስኪ ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው በ18 ዓመት ከ2 ወሩ ነበር።

.ኪሊያን ምባፔ እ.አ.አ ነሐሴ 31/ 2017 ፈረንሳይ በ21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ኔዘርላንድስን 4 ለ 0 ስታሸንፍ ለአገሩ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ።

.እ.አ.አ መጋቢት 25 በ2018 ፈረንሳይ በወዳጅነት ጨዋታ ሩሲያን 3 ለ 1 ስትረታ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

.በሩሲያ አስተናጋጅነት እ.አ.አ 2018 ባሰናዳችው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ሶስት የነበረችው ፈረንሳይ ፔሩን 1 ለ 0 ስታሸንፍ ብቸኛዋን ያስቆጠረው ኪሊያን ምባፔ ነው። በ19 ዓመቱ ግብ ለፈረንሳይ በዓለም ዋንጫው ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች መሆን ቻለ።

.በዓለም ዋንጫ ጨዋታው በጥሎ ማለፉ ፈረንሳይ አርጀንቲናን 4 ለ 3 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው ባለፈችበት ጨዋታ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ከብራዚላዊው ዝነኛ ተጫዋች ፔሌ  በመቀጥል በዓለም ዋንጫው በእድሜ ትንሹ ሁለት ግብ አስቆጣሪ አድርጎታል። ፔሌ ስዊድን ባሰናዳችው ስድስተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ብራዚል አስተናጋጇን አገር በፍጻሜው 5 ለ 2 ስትረታ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር እድሜው 17 ዓመት ከ 249 ቀን ነበር።

. ኪሊያን ምባፔ “ከፔሌ በመቀጠል ሁለተኛ መሆኔ ትልቅ ክብር ነው፤ ነገር ግን ነባራዊ ሁኔታዎችን መረዳት በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል። ፔሌ በሌላ ደረጃ ላይ የሚገኝ ትልቅ ተጫዋች ነው” ሲል ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያየት ገልጿል።

. እ.አ.አ ሐምሌ 15/2018 በሉዚኒስኪ ስታዲየም በዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ፈረንሳይ ክሮሺያን 4 ለ 2 ስታሸንፍ ኪሊያን ምባፔ ከ22 ሜትር ርቀት ላይ አክርሮ የመታት ካስ በአስደናቂ ሁኔታ መረብ ላይ አርፋለች። ምባፔ ያስቆጠራት ከፔሌ በመቀጠል በዓለም ዋንጫ ፍጻሜው ግብ ያስቆጠረ ሁለተኛ ተጫዋች አድርጎታል። ፔሌም በማህበራዊ ትስስር “እንኳን የዓለም ዋንጫ የታሪክ ተቋዳሽ ለመሆን በቃህ” አድናቆቱን ገልጾለታል። ምባፔ በዓለም ዋንጫው ወጣት ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።

.በኳታር አስተናጋጅነት በተካሄደው እና ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ስምንት ግቦችን በማስቆጠር የውደድሩ ከፍተኛ የግብ አስቆጣሪነት ሽልማትን አግኝቷል።

.በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል። ይህም እ.አ.አ በ1966 እንግሊዝ ባሰናዳችው ስምንተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በፍጻሜው ጀርመን (በወቅቱ መጠሪያዋ ምዕራብ ጀርመን) 4 ለ 2 ስታሸንፍ ሶስት ግቦች ካስቆጠሩት ሰር ጂኦፍ ሀረስት ጋር በመቀጠል በፍጻሜ ጨዋታ ሀትሪክ የሰራ ሁለተኛ ተጫዋች መሆን ችሏል።

.ኪሊያን ምባፔ በፍጻሜው ጨዋታ ያሳየው አስደናቂ ብቃት በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት እና ሙገሳ እንዲጎርፍለት አድርጓል።

.በሁለት የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች አራት ግቦችን ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ ጽፏል።

.በሁለት ዓለም ዋንጫዎች በ14 ጨዋታ 12 ግቦችን በማስቆጠር ከምንጊዜም የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ከብራዚላዊው ዝነኛ ተጫዋች ፔሌ ጋር መስተካከል ችሏል።

. በዓለም ዋንጫው 24 ዓመት ሳይሞላው 12 ግቦችን ያስቆጠረ ወጣት ተጫዋች መሆንም ችሏል

.በዓለም ዋንጫው የፍጻሜ ጨዋታ ፈረንሳይ በአርጀንቲና በመለያት 4 ለ 2 ከተሸነፈች በኋላ በከፍተኛ ስብራት ውስጥ የነበረው ኪሊያን ምባፔ የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከመቀመጫው ወርደው ወደ ሜዳ በመግባት ሲያጽናኑት ታይቷል።

. “አንድ ተጫዋች በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ሀትሪክ ሰርቶ ዋንጫ አለማንሳት የማይጠበቅ ክስተት ኪሊያን ምባፔ የገጠመው ይሄ ነው” ሲሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከጨዋታው በኋላ ባወጧቸው ዘገባዎች ገልጸዋል።

. የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ከኳታር ተነስቶ ከትናንት በስቲያ ማምሻውን ፓሪስ ሲደርስ ባልጠበቀ ሁኔታ በሺዎች በሚቆጠሩ ፈረንሳውያን ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

. በፓላስ ኮን ኮርድ በነበረው ደማቅ የአቀባባል ስነ ስርዓት በፍጻሜው ጨዋታ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሀትሪክ የሠራው ኪሊያን ምባፔ ከፊት ሆኖ ሰላም ሲሰጥ ታይቷል።

. ኪሊያን ምባፔ በአጠቃላይ ለብሔራዊ ቡድን እና ለክለብ ባደረጋቸው 362 ጨዋታዎች 253 ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ አስደናቂ የሚባል የግብ ክብረ ወሰን አለው።

. የዓለም ዋንጫ ጨምሮ በክለብ እና በብሔራዊ ቡድን በድምሩ 13 ዋንጫዎችን በማንሳት በወጣት እድሜው ከፍተኛ የሚባል ስኬትን ተጎናጽፏል።

. ምባፔ እስከ አሁን ያለነሳው ዋንጫ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ነው።

.ኳስን በማንከባለል ብቃቱ፣ በአስገራሚ ፍጥነቱ እና አጨራረሱ አድናቆት እየተቸረው ያለው ኪሊያን ምባፔ ከሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ የታላቅ አገር ካስ ተጫዋችነት ዙፋን እና ማዕረግ ይረከባል የሚሉት ብዙሃኑ ናቸው።

.ምባፔ ለአሜሪካው ዕለታዊ ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ በቅርቡቡ በሰጠው ቃለ መጠይቅ “ ሁልጊዜ እንደምለው ስለ ሁሉም ነገር አልማለሁ ምንም በራሴ ላይ ያስቀመጥኩት ገደብ የለም፤ አዲስ ትውልድ ነው ሮናልዶ እና ሜሲ ካልክ እዛው ትቆማለህ። የሆነ የሚተካቸው የሆነ ሰው መፈለግ አለብን አዲስ ሰው መፈለግ አለብን” ሲል ስለ ሜሲ እና ሮናልዶ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል።

. “ቀጣዩን ባለንዶር የማሸነፈው እኔ ነኝ ማሸነፍ ይገባኛል” ሲልም ተናግሯል።

.ፈረንሳዊ ወጣት ኪሊያን ምባፔ ቀጣዩ የምንጊዜም የዓለማችን ኮከብ ተጫዋች ይሆን? የሜሲ እና የሮናልዶን ዙፋን ይረከባል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ቀጣዮቹ ዓመታት ምላሽ ይሰጣሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም