ቀጥታ፡

ታሪክ ሰሪው የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን አገሩ ሲገባ የጀግና አቀባበል ተደረገለት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 12/2015 በኳታር አስተናጋጅነት በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የአፍሪካዊቷ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን አገሩ ሲገባ የጀግና አቀባበል ተደረገለት።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሞሮኳውያን ቡድኑን ለመቀበል ትናንት በመዲናዋ ራባት አደባባይ ወጥተዋል።

ተጫዋቾቹም በራባት ጎዳናዎች በክፍት አውቶቢስ በመዟዟር ከደጋፊዎች ጋር ደስታቸውን ገልጸዋል።

የሞሮኮ ንጉስ መሐመድ ስድስተኛም ለተጫዋቾቹ በቤተ መንግስት አቀባበል እንዳደረጉላቸው ሞሮኮ ወርልድ ኒውስ በድረ ገጹ አስፍሯል።

ንጉስ መሐመድ በሞሮኮ አልጋ ወራሽ ልዑል ሙላህ ኤል ሀሰን እና በልዑል ሙላይ ራሺድ ታጅበው ለተጫዋቾቹና ለአሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ የሜዳሊያ (Royal wissams) ሽልማት አበርክተዋል።

ለሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፋውዚ ሌክጃ እና ለአሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ የሞሮኮ መንግስት ልዩ ግልጋሎት ለሰጡ ዜጎች እና ወታደሮች የሚሸልመውን “ኦርደር ኦፍ ዘ ስሮን ዊሳም” ሁለተኛ ደረጃ (Second class Order of the Throne Wissam (Commander) የክብር ሽልማት አበርክተውላቸዋል።

ንጉስ መሐመድ ስድስተኛ ለአምበሉ ሮማን ሳይስ፣ አሽራፍ ሀኪሚ፣ ሀኪም ዚዬች፣ሶፊያን ቡፋል እና አዝዲን ኡናሂ ጨምሮ ለሌሎች ተጫዋቾና የቡድኑ አባላት “ኦርደር ኦፍ ዘ ስሮን” (ኮማንደር) ሶስተኛ ደረጃ (Third class Order of the Throne Wissams (Officer) የክብር ሽልማት ሰጥተዋል።

ሞሮኮ ከሕዳር 11 እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በውድድሩ ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈች የመጀመሪያ አፍሪካዊት አገር በመሆን አዲስ ታሪክ መስሯቷ ይታወሳል።

የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ፖርቹጋልን፣ቤልጂየም እና ስፔንን ማሸነፍ ችላለች።

የአትላስ አንበሶች የማይበገረው የማሸነፍ መንፈሳቸው እና አገር ወዳድነታቸው ከፍተኛ አድናቆት አስገኝቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም