ቀጥታ፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከቴሌ ሞባይል ደቡብ ሱዳን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያጋር የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 12/2015 ኢትዮ ቴሌኮም ከቴሌ ሞባይል ደቡብ ሱዳን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅርቦትንና በሌሎች ተያያዥ መስኮች በትብብር መስራት የሚያስችለውን የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ የተፈረመው በኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ የተመራ ልዑካን ቡድን በደቡብ ሱዳን ጉብኝት ባካሄደበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።

ስምምነቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ እና የደቡብ ሱዳን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አይሸሹም ተካ ፈርመዋል።

May be an image of 2 people and indoor

ትናንት የተፈረመው ስምምነት ሁለቱ አካላት በዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መገናኛ መስመር፣በቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ፣የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅርቦት እና በሌሎች ተያያዥነት ባላቸው አገልግሎቶች በትብብር ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ከኢትዮ ቴሌኮም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የቴሌ ሞባይል ደቡብ ሱዳን ኩባንያ በአገሪቷ በቴሌኮም አገልግሎት እንዲሁም በኢንፎርሜሽን፣ኮምዩኒኬሽን እና ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ የሚሰራ ነው።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ የተመራው ልዑክ በደቡብ ሱዳን በነበረው ቆይታ ከደቡብ ሱዳን የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙዩኒኬሽን፣ ቴክኖሎጂ እና የፖስታ አገልግሎት ሚኒስትር ማይክል ሉኤት እና ከሌሎች የደቡብ ሱዳን ሚኒስትሮች እና አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

ውይይቱ በደቡብ ሱዳን ያለውን የቴሌኮም መሰረተ ልማት ፍላጎት እንዲሁም በሁለቱ ሀገሮች በትብብር ሊከናወኑ ስለሚችሉ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ያተኮረ መሆኑን ቴሌ ሞባይል ደቡብ ሱዳን ገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት የደቡብ ሱዳን መንግስት የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነት እና የዋጋ ተመጣጣኝነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ላለው ጥረት ድርጅታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ሱዳን ያለውን የቴሌኮም ገበያ ለመቃኘት ያለውን ፍላጎት በማድነቅ ድርጅቱ በዘርፉ ለሚያደርገው ተሳትፎ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጉብኘቱም ወቅት ልዑካን ቡድኑ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ጋር በደቡብ ሱዳን ባላቸው የቢዝነስ እንቅስቃሴ እና ተሞክሮ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው መረጃው ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም