የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በክረምት ወቅት ያሠለጠናቸውን 60 ባለ ልዩ ተሰጥኦ ወጣቶች ሊያስመርቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በክረምት ወቅት ያሠለጠናቸውን 60 ባለ ልዩ ተሰጥኦ ወጣቶች ሊያስመርቅ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በክረምት ወቅት ያሠለጠናቸውን 60 ባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊ ወጣቶች ሊያስመርቅ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ምርቃቱን በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሐሚድ እንዳሉት፤ ተመራቂ ወጣቶች በ2014 በክረምት ወቅት ተለይተው ያላቸውን ልዩ ተሰጥኦ የሚያሳድጉበትን ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡
ባለልዩ ተሰጥኦ ወጣቶች ታህሳስ 22 ቀን 2015 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም የሚመረቁ ሲሆን ከታህሳስ 13 ቀን ጀምሮ የፈጣራ ስራዎቻቸውን በኤግዚቢሽን መልክ ያቀርባሉ ብለዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የፈጣራ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ልማትና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰላምይሁን አደፍረስ ልዩ ተሰጥኦ ያለቸው ታዳጊዎች የተለያዩ ድጋፍና ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
በዚህም የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ፕሬዘዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር ስራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ አቅርቦት ላይ የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች የሚመለከት በማህበሩ የተዘጋጀ "ዘለላ" የተሰኘ ፕሮግራም ይቀርባል ብለዋል፡፡
በዚህም መድረክ የኢትዮጵያ ባለሃብቶች በመሳተፍ በጉዳዩ ላይ የሚመክሩ ሲሆን ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ከፋይናንስ ምንጮች ጋር ለማስተሳሰር ያግዛል ብለዋል፡፡