ቀጥታ፡

የቡና አምራቾችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል የሚሰራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ተመሰረተ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 11/2015 የቡና አምራቾችን ተጠቃሚነትን ለማሻሻል የሚሰራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር በይፋ ተመስርቷል፡፡

ማህበሩን የመሰረቱት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በቡና ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አምስት ማህበሮች ናቸው፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሁሴን አምቦ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ማህበሩ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ህጋዊ ሰውነት ማግኘቱን ገልፀዋል፡፡

ማህበሩ በዋናነት ቡና አምራቾች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶች በመለየት የሚፈቱበትን አግባብ ለመፍጠር እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ቡና የዓለም አቀፍ ጥራትን በጠበቀ መልኩ እንዲመረት ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር  እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ይህን በማድረግም ኢትዮጵያ ከቡና የምታገኘው ገቢ እንዲሻሻል የበኩሉን ሚና ይወጣል ነው ያሉት፡፡

የቡና አምራቾች ለህገ ወጥ ደላሎች ያላቸውን ተጋላጭነት በመቀነስ ከምርታቸው የሚገባቸውን ገቢ እንዲያገኙ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡

ማህበሩን የመሰረቱት የኢትዮጵያ ቡና አልሚዎች፣ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ፤የኢትዮጵያ ሴቶች ቡና ማህበር ፤የኦሮሚያ ቡና አዘጋጆችና አቅራቢዎች ማህበር፣ የሲዳማ የቡና አዘጋጆች አቅራቢዎች ማህበር እና የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ክልላዊ መንግስት የቡና አቀነባባሪዎችና አቅራቢዎች ማህበር መሆናቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም